ዘካቱል ፊጥር በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ማለትም በሴትም ፣ በወንድም ፣ ነፃ በሆነም ፣ ባሪያ ነሆነም ፣ በወጣቱ ፣ በአዛውንቱ ላይ ሁሉ ግዴታ የሆነ የምፅዋት አይነት ነው። የሚሰጠውም ሊረዱ የሚገባቸው ሰዎች ሲሆን ረመዷን ተከትሎ በሚመጣው በሸዋል የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው።
ኢብን አባስ አሉ፡ “የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዘካቱል ፊጥርን ለፆመኛ ሰው ትርፍ ንግግር ወይም ጥቅም ለሌለው ተግባር እና ፀያፍ ንግግር ወይም ባህሪ መፅጃ ይሆን ዘንድ እና ድሆችን የሚመገቡበት መንገድ ይሆን ዘንድ ግዴታ አደረጉት። ከሶላቱ (ከኢድ ሶላት) በፊት የሰጠ ሰው ቅቡልነተ ያለው ዘካ ነው። ከስግደቱ በኋላ የሰጠ ሰው የተለመደው የሶደቃ አይነት ነው።” (አቡዳውድ እና ኢብኑ ማጃ)

ዘካቱል ፊጥር የኢድ ሶላት ከመስገድ በፊት መሰጠት እንደሚገባ ይህ ሐዲስ ግልፅ አድርጎታል። በዚህ ቀን ማድረጉ በላጭ ቢሆንም ከኢድ ቀን በፊት አንድ ወይም ሁለት ቀን ቀደም ብሎ መስጠት ይቻላል።
የዚህ ዘካ መጠን አንድ ሰኢ ሲሆን ከአራት ሙዳድ (ነ.ቁ ሙድ አንድ እፍኝ) ጋር አቻ፤ እኩል ነው። የሚሰጠውም በሐገሪቱ ለምግብነት የሚጠቀሙት ነገር መሆን አለበት። አቡ ሰኢድ እንዲህ አለ፡
“የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በመካከላችን በነበሩ ጊዜ በእያንዳንዱ ሰው በወጣቱ እና በሽማግሌው ፣ በባሪያው እና ነፃ በሆነው ሰው ስም ዘካቱል ፊጥር አንድ ሰኢ ማሽላ (በቆሎ) ወይም አይብ ወይም አንድ ሰኢ ገብስ ወይም አንድ ሰኢ የደረቀ ተምር ወይም አንድ ሰኢ ዘቢብ እንሰጥ ነበር።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ዘካቱል ፊጥር የሚሰጠው ከምግብ አይነቶች ነው። ገንዘብ ሊሰጥ አይገባም። ይሄን ለማድረግ አስገዳጅ ነገር እስካልኖረ ድረስ። በገንዘብ መክፈል የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና የሶሃቦቹ ተግባር አይደለምና ነው።
ዘካቱል ፊጥር ለቀኑ የሚሆን በቂ የሆነ ምግብ በሌለው ሰው ላይ ግዴታ አይደለም። ለቀኑ የሚሆን በቂ ምግብ ኖሮት ይህን ዘካ በመክፈል፤ ይህ ለእሱ በቂ ነው።

Share