ውድ ሙስሊም ወጣቶች!
በዚህ ወሳኝ የሕይወት ምዕራፍ ላይ የምትገኙ ሙስሊም ወጣቶች ልባዊ ሰላምታችን እና ውዴታችን ይደረሳችሁ። ይህ ጊዜ የብርታት፣ የጉጉት፣ የእውቀት ፍለጋ እና ለወደፊት ህይወታችሁ መሰረት የምትጥሉበት ወርቃማ ወቅት ነው። ይህን ጊዜ በእስልምና ብርሃን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደምትችሉ አንዳንድ ቁም ነገሮችን እናካፍላችሁ።
ዓለም በፍጥነት እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት ሙስሊም ወጣቶች ላይ የሚደርሱ ተግዳሮቶች እየተባባሱ መጥተዋል። ዘመናዊውን ሕይወት ከእስልምና ትምህርቶች ጋር አጣጥሞ መጓዝ ብዙ ጊዜ ከባድ ሊመስል ይችላል።
ሆኖም ይህ መልዕክት ትርጉም ያለው እና ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ይሆናችኋል ብለን እናምናለን። ይህ ጽሑፍ ሙስሊም ወጣቶች ሕይወታቸውን በቁርአን እና በሱና መርሆዎች መሰረት እንዴት መምራት እንደሚችሉ ለማመላከት ያለመ ሲሆን የእምነት ፣ የባህሪ እና የማህበረሰብን አስፈላጊነት ወ.ዘ.ተ ያጎላል።
ሙስሊም ወጣቶች እንደመሆናችሁ ማንነታችሁን ተረዱ
ሙስሊም ወጣት መሆን መታወቂያ ብቻ አይደለም፤ በእምነት ላይ የተመሰረተ የአንድን ሰው ማንነትን ያካትታል። ቁርአን እንዲህ ሲል ያስታውሰናል፡-
አል-ቁርአን
ሱረቱል ሑጅራት 49:13
“በእርግጥ አላህ ዘንድ በላጫችሁ አላህን ፈሪያችሁ ነው።”
ይህ አንቀጽ የአንድ ሰው ዋጋ የሚወሰነው በማህበረሰባዊ መመዘኛዎች ሳይሆን አላህ በመፍራት እና በመልካም ስራ መሆኑን ይገልፃል።
ማንነታችሁን በኩራት ተቀበሉ፡ የእስልምና እውቀታችሁን የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ተሳተፉ፡፡ ለምሳሌ ትምህርቶችን መከታተል ፣ የእስልምና መጽሐፍት ማንበብ እና በማህበራዊ ሁነቶች ላይ በንቃት መሳተፍ ናቸው። እምነታችሁን በጥልቀት መረዳት በዚህ አለምም ሆነ በመጭው አለም ህይወት ለስኬት እንድትበቁ ይረዳችኋል።
ከኃጢአት መራቅ እና በጎ ስራ መሥራት
የሕይወታችሁ ዋና መሰረት ጠንካራ እምነትና አላህን መፍራት ሊሆን ይገባል። አላህ ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን ቻይ እንደሆነ አስታውሱ። በሁሉም ሁኔታዎች እርሱን ብቻ ተመኩ። ከእርሱ እርዳታን ጠይቁ። ትክክለኛውን መንገድ እንዲመራችሁ ሁል ጊዜ ዱዓ አድርጉ። የአላህን ትዕዛዛት ጠብቁ ፣ ከእርሱ ቁጣ የሚያስከትሉ ነገሮችን ሁሉ ራቁ።
ወጣነት የፈተና ጊዜ እንደሆነ እንረዳለን። በዚህ ወቅት ስሜቶች ሊበረቱ፣ ጓደኞችም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ነገር ግን አላህን በመፍራትና ትክክለኛውን መንገድ በመከተል እነዚህን ፈተናዎች ማለፍ ትችላላችሁ።
ከአላህ መንገድ እንድታፈነግጡ ከሚያደርጓችሁ ነገሮች ሁሉ ራቁ። ሀሜት ፣ ወሬ ማውራት ፣ ሌሎችን መናቅ ፣ ሀራም የሆኑ ነገሮችን መመልከትና መስማት ፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀም እና የመሳሰሉትን ክፉ ተግባራት ተጠንቀቁ።
በተቃራኒው መልካም ስራዎችን በመስራት ላይ ትኩረት አድርጉ። ሶላትን በወቅቱ ስገዱ ፣ ቁርአንን አንብቡና አስተንትኑ ፣ ለወላጆቻችሁ መልካም ሁኑ ፣ ችግረኞችን እርዱ ፣ ሰዎችን በደግነት ተናገሩ። መልካም ስራዎች ልባችሁን ያፀዳሉ ፣ ስኬታችሁን ያፋጥናሉ ፣ በአኼራም ትልቅ ምንዳ ያስገኙላችኋል።
የሶላትን ወቅት ጠብቆ መስገድ
ሶላት የእስልምና ዋና ምሰሶ ሲሆን አስፈላጊነቱም ሊገመት አይችልም። ሶላት በምትሰግዱበት ጊዜ ከአላህ ጋር ትገናኛላችሁ ፣ መመሪያ ትፈልጋላችሁ እና በልባችሁ ውስጥ ሰላም ታገኛላችሁ። ቁርአን እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
ሱረቱ ኑር 24:56
“ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፤ ዘካንም ስጡ፤ መልክተኛውንም ታዘዙ፡፡ ሊታዘንላችሁ ይከጀላልና።”
አምስቱን የዕለት ሶላቶች ወቅታቸውን ጠብቃችሁ መስገድ የዘወትር ልማዳችሁ ይሁን። እነዚህ የሶላት ጊዜያት ግዴታን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን ከአላህ ጋር ለመገናኘት እና የምታሰላስሉበት እድል አድርጋችሁ ተጠቀሙባቸው። በሶላት ላይ ቀጣይነት መኖር ስነ-ስርዓትን ያዳብራል፤ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ዓላማ እንዲኖራችሁ ያዳርጋል።
እውቀት መፈለግ
እውቀትን መፈለግ የሚበረታታ ተግባር ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ የተቀደሰ እና ግዴታ የሆነ ተግባር ነው። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሱንኑ ኢብኑ ማጃህ)
“እውቀትን መፈለግ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው።”
ይህ ግዴታ ሃይማኖታዊም ይሁን ዓለማዊ ትምህርት የዕድሜ ልክ ጥረት መሆን እንዳለበት ያሳያል።
ጊዜ ወስዳችሁ በመማር ይህንን ግዴታ ፈፅሙ። የእስልምና መጽሐፍት አንብቡ ፣ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን አጥኑ፤ እራሳችሁንም ሆነ ማህበረሰብህን የሚጠቅሙ ክህሎቶችን አዳብሩ። እውቀት በዙሪያችሁ ያለውን ዓለም በአስተውሎት እንድትመለከቱ ያስችላችኋል ፣ ተግዳሮቶችን እንድትፈቱ እና በአዎንታዊ መልኩ ለህብረተሰቡ አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ያስችላችኋል፡፡
እውቀት በእስልምና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የእውቀትን ጥቅም በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተምረዋል። ቁርአንም በተደጋጋሚ እውቀትን እንድንፈልግ ያበረታታል።
ሙስሊም ወጣቶች ይህን ወርቃማ እድል ተጠቅማችሁ በሃይማኖታችሁም ሆነ በዱንያዊ ጉዳዮቻችሁ ላይ እውቀት ለመቅሰም ትጉ። ትምህርታችሁን በጥንቃቄ ተከታተሉ፣ መጻሕፍትን አንብቡ፣ የእውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ። የተማራችሁትንም በተግባር ለማዋል ሞክሩ። እውቀት ለነፍሳችሁ ብርሃን፣ ለህይወታችሁ መመሪያ ነው።
ጊዜን በአግባቡ መጠቀም
የወጣትነት ጊዜ ውድና የማይመለስ ሃብት ነው። ይህን የወጣትነት ጊዜ በከንቱ ማሳለፍ በኋላ ትርፉ ፀፀት ነው። ለትምህርታችሁ ፣ ለቤተሰባችሁ ፣ ለሃይማኖታችሁ እና ለግል እድገታችሁ ጊዜ መድቡ። ጠቃሚ በሆኑ ስራዎች ላይ ተሳተፉ ፣ ስፖርት ስሩ ፣ ጤናማ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችን ምረጡ። ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ስኬትን ያረጋግጣል። ዛሬ የምትዘሩት ለነገ ህይወታችሁ ፍሬ ነው።
መልካም ባህሪ (አኽላቅ) መላበስ
በእስልምና መልካም ባህሪ መላበስ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ቁርአን እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ፈትህ 68:4)
“በእርግጥ አንተ በታላቅ ስነ ምግባር ላይ ነህ።”
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በሕይወታቸው ይህንን አሳይተዋል፡፡ ህይወታቸውን የኖሩትም በደግነት ፣ በታማኝነት እና ለሌሎች በማዘን ነው።
የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ስነ-ምግባርን እና ግብረገብን ሲያበረታቱ እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሐኪም)
‹‹እኔ የተላኩት መልካም ስነ-ምግባርን ላሟላ ነው፡፡››
በዕለት ተዕለት ግንኙነታችሁ ውስጥ እነዚህን እሴቶች ለመላበስ ሞክሩ። ሌሎችን በአክብሮት ያዙ ፣ ትዕግስትን ተለማመዱ፤ በጎ ተግባራትንም አከናውን። ባህሪያችሁ ከእስልምና አስተምህሮቶች ጋር የሚስማማ መሆኑን አረጋግጡ።
የወላጆች እና የሽማግሌዎችን ምክር መቀበል
ወላጆች ለእናንተ ከማንም በላይ የሚጨነቁና መልካም ነገር የሚመኙላችሁ ናቸው። የህይወት ልምድ ያላቸው ሽማግሌዎችም ብዙ ሊያስተምሯችሁ ይችላሉ። የእነዚህን ሰዎች ምክር በክብር ተቀበሉ። ስህተት ከሰሩ በረጋ መንፈስ አስተካክሏቸው። ትዕቢትን አስወግዳችሁ ሁል ጊዜ ለመማር ዝግጁ ሁኑ።
ማህበራዊ ተሳትፎ
እስልምና የማህበረሰብን አስፈላጊነት ያጎላል። ቁርአን ስለ ኡማ ጽንሰ-ሀሳብ ያስተምራል፡፡ አማኞች ወንድማማቾች መሆናቸውን ይገልፃል። ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሶሒህ ሙስሊም)
“አማኞች በአንድ አካል ይመሳሰላሉ፤ አንዱ የአካል ክፍል ሲታመም መላው አካል ይታመማል።”
በማህበራዊ ሁነቶች እና ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ ትስስርን ያጠናክራል፤ ትብብርን ያጎለብታል። በማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ ተሳተፉ፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በፈቃደኝነት ስሩ። ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ለራሳችሁ እና ለሌሎች አዎንታዊ እና የበለፀገ አካባቢ ለመፍጠር አስተዋፅኦ አድርጉ።
እናንተ ሙስሊም ወጣቶች የነገ ማህበረሰብ ተረካቢዎች ናችሁ። ከወዲሁ ለእምነታችሁ ፣ ለሐገራችሁ ፣ ለወገኖቻችሁ እና በአጠቃላይ አለም ጠቃሚ ለመሆን ተዘጋጁ። በጎ ፈቃደኛ በመሆን ሰዎችን እርዱ፣ አካባቢያችሁን ጠብቁ ፣ በስራችሁ ላይ ታማኝ ሁኑ። በህብረተሰባችሁ ውስጥ መልካም ለውጥ ለማምጣት ተነሱ።
እስልምና ማህበራዊ ፍትህን እና ማህበረሰቡን ማገልገል ይደግፋል። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) የተጨቆኑ ሰዎች ሻምፒዮን ነበሩ፡፡ ስለሆነም የእሳቸው ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን እኛ ሙስሊም ወጣቶች ፈለጋቸውን በመከተል የሰሯቸውን ተግባራት መስራት ይኖርብናል።
ሰብአዊ ድጋፍ ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ወይም ማህበራዊ ፍትህን መደገፍን የመሳሰሉ ትኩረት ብናደርግባቸው ወይም መፍትሄ ቢያገኙ የምትሏቸውን ጉዳዮችን ለዩ። በንቃት ተሳተፉ ፣ ለማህበረሰቡ መሻሻል ችሎታችሁን እና እውቀታችሁን አበርክቱ። ይህ ድርጊት የእስልምናን አስተምህሮት የሚያንፀባርቅ እና የሙስሊም ወጣቶች ተሳትፎ የሚያሳድግ ነው።
ቴክኖሎጂን በጥበብ መጠቀም
በዚህ ዘመን ብዙ ፈተናዎች አሉ። የቴክኖሎጂ እድገት በአንድ በኩል ብዙ ጥቅሞች ሲኖሩት በሌላ በኩል ደግሞ ለተለያዩ አደጋዎች ሊያጋልጠን ይችላል። በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ረገድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ጊዜያችሁን ከሚሰርቁ እና ከእምነታችሁ ጋር ከሚጋጩ ነገሮች ራቁ። በምትጠቀሙባቸው ነገሮች ላይ አስተዋይ ሁኑ።
ቴክኖሎጂ በአሁኑ ጊዜ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ለመማር እና ለመዝናናት ሰፊ እድሎችን የሚሰጥ ቢሆንም የተሳሳተ መረጃ እና ትኩረትን የሚከፋፍሉ ተግዳሮቶች እና መጥፎ ገፅታዎች አሉት። ቴክኖሎጂን በንቃት እና በጥበብ ተጠቀሙ።
ዲጂታል መሳሪያዎችን ለትምህርት ፣ የእስልምና መልዕክት ለማስተላለፍ እና ማህበረሰቡን ለማንቃት እና ለሌሎች በጎ አላማዎች ተጠቀሙበት። ይሁንእንጅ ስለምትጠቀሙበት እና ስለምታተላልፉት ይዘት ማወቅ አለባችሁ። አሏህ እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
ሱረቱል ኢስራዕ 17:36
“በእሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል።”
ጠቃሚ ይዘትን መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ይዘቶች መለየት ለግል እድገታችሁ ወሳኝ ነው።
ጽናት እና ትዕግስት ማዳበር
ሕይወት ብዙ ተግዳሮቶች ፣ መሰናክሎች እና ችግሮች አሏት። ቁርአን በአስቸጋሪ ጊዜያት ትዕግስት እና ጽናት እንዲኖረን ይመክራል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
አል-ቁርአን
ሱረቱ ነህል 16:127
“ታገስም፤ ትዕግስትህም በአላህ እንጂ በሌላ አይደለም።”
ተግዳሮቶችን የእድገት እድሎች አድርጋችሁ ተቀበሉ።
ከውድቀቶች በመማር እና አዎንታዊ አመለካከትን በመጠበቅ ጽናትን አዳብሩ። እያንዳንዱ ፈተና ወደ አላህ ሊያቀርባችሁ እንደሚችል አስታውሱ።
ልዩነትን መቀበል፡ በልዩነት ውስጥ አንድነት
የሙስሊም ኡማ የተለያዩ ባህሎች ፣ ቋንቋዎች እና ወጎች ያሉት ነው። ቁርአን ይህንን በሚያምር ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-
አል-ቁርአን
ሱረቱል ሑጅራት 49:13
“እናንተ ሰዎች ሆይ! ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤ ትተዋወቁም ዘንድ ጎሳዎች እና ነገዶች አደረግናችሁ።”
በመዝሃብ ፣ በአቂዳ ፣ በአመለካከት ወዘተ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦች ጋር ስትገናኙ ልዩነቱን ተቀበሉ። መግባባትን እና አንድነትን የሚያበረታቱ የሃሳብ ልውውጥ እና ማህበራዊ ሁነቶች ላይ ተሳተፉ። ይህን በማድረጋችሁ እስልምና የሚያስተምረውን አክብሮት ፣ ርህራሄ እና ወንድማማችነትን ታዳብራላችሁ።
ማጠቃለያ
ውድ ሙስሊም ወጣቶች! ይህ የእናንተ የእድገት ዘመን ነው፤ በአግባቡ ተጠቀሙበት። እውቀትን በመፈለግ ፣ በጎ ስራዎችን በመስራት ፣ ጊዜያችሁን በአግባቡ በመጠቀም ፣ የወላጆቻችሁን እና የሽማግሌዎችን ምክር በመቀበል ፣ በራስ በመተማመን ፣ ጠንካራ እምነት በመያዝ እና ለህብረተሰባችሁ ጠቃሚ በመሆን የተሳካ እና አላህን የሚያስደስት ህይወት መኖር ትችላላችሁ።
ሙስሊም ወጣቶች በቁርአን እና በሱና ውስጥ የተዘረዘሩትን መርሆዎች በመከተል እጅግ አርኪ እና ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር ትችላላችሁ። ማንነታችሁን ተቀበሉ ፣ ሶላት ወቅቱን ጠብቀችሁ ስገዱ ፣ እውቀት ፈልጉ ፣ መልካም ባህሪን ተላበሱ ፣ ማህበራዊ ተሳትፎ ይኑራችሁ ፣ ህይወታችሁን በድስፕሊን ምሩ።
ጽናት ይኑራችሁ ፣ ቴክኖሎጂን በጥበብ ተጠቀሙ ፣ ልዩነትን በመቀበል በማህበራዊ ጉዳዮች የራሳችሁን አስተዋፅኦ አድርጉ። ሕይወት በችግሮ የተሞላ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እምነታችሁን እንደ መሪ ኮምፓስ በመጠቀም ጉዟችሁን የተቃና እና የተሳካ አድርጉ።
በመጨረሻም አላህ ሁላችንንም ቀጥተኛውን መንገድ እንዲመራን እና መልካም ስራዎችን ለመስራት እንዲያግዘን እንለምነዋለን። ሙስሊም ወጣቶች አላህ ከክፉ ነገር ሁሉ እንዲጠብቃቸው ፣ ሕይወታችሁን በአስተምህሮቱ መሰረት ለመምራት የሚያስችላችሁን ጥበብ እንድያድላችሁ እንለምነዋለን።

Share