ህይወት ያለ ኢማን ትርጉም የላትም! ከሁሉም ጭንቀታምና ደስታ አልባዎች ማለት የኢማንን ጣዕም ያልቀመሱና የየቂንን (በአሏህ እርግጠኛ የመሆንን) ምንነት የማያውቁ ናቸው።
እነዚህ ሁሌም ጭንቀት ፣ ንዴት ፣ ውርደትና ጥበት ውስጥ ናቸው።
አል-ቁርአን
ሱረቱ ጣሃ 20:124
«ከግሳፄም የዞረ ሰው ለርሱ ጠባብ ኑሮ አለው።»
የአለማቱ ጌታ በሆነው አሏህ ከማመን ውጭ ነፍስን የሚያስደስታት ፣ የሚያጠራት የሚያነፃት ፣ ጭንቀቷንና ጥበቷንም የሚያስወግድላት ነገር የለም።
ካለም ኢማን ህይወትና ጣዕም ሊኖራት አይችልም።
እምነት (ኢማን) አልባዎች ከችግር መላቀቂያና እራሳቸውን ከጭንቀት ፣ የነፋስ ፅልመትና ጉዳት ማረፊያ አይነተኛ ዘዴያቸው ካላመኑ እራሳቸውን ማጥፋት ነው።
ኢማን የሌለባት ህይወት ጥፉ እና ክፉ ነች። የአሏህን የህይወት ጎዳና የሚቃረኑት የሚከተላቸው ዘላለማዊ እርግማን ምንኛ የከፋ ነው።
አል-ቁርአን
ሱረቱል አንአም 6:110
«በመጀመሪያም ጊዜ በርሱ እንዳላመኑ ሁሉ ልቦቻቸውን እና ዓይኖቻቸውን እናገላብጣለን ፤ በጥመታቸውም ውስጥ የሚዋልሉ ሲሆኑ እንተዋቸዋለን።»
አዕምሮ ከረጅም እልህ አስጨራሽና ለብዙ ዘመናት ከቆየ ጥናት በኋላ የደረሰበትን የጣኦት ከንቱነት ፣ የክህደትን እርጉምነት እና ውሸተኝነት እንዲሁም የመልእክተኞችን እውነተኝነት እና የአሏህን ሃቅነት ፣ ንግስናና ምስጋና የሱ እንደሆኑና በሁሉም ነገር ላይ ቻይ መሆኑን አይቶ ዓለም በሙሉ በአሏህ ብቸኛ አምላክነት የሚያምንበት ጊዜው አሁን ነው።
ደስታህ ፣ ዕረፍትህና እርጋታህ በኢማንህ ጥንካሬና ድክመት ፤ ትኩሰነት እና ቅዝቃዜ ልክ ይሆናል።
አል-ቁርአን
ሱረቱ ነህል 16:97
«ለወንድ ወይም ሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን ፤ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።»
ይህችም መልካም ኑሮ መገለጫዋ ለጌታቸው መልካም ቃል ኪዳን የነፍሶቻቸው መረጋጋት ፣ ፈጣሪያቸውን በመውደድ የልቦቻቸው ፅናት ፣ ከጥመት ጎዳና የውስጣቸው መጥራት ፣ በችግር ጊዜ ያላቸው ጥንካሬ ፣ የአሏህ ውሳኔ ሲፈጸም የልቦቻቸው አለመጨነቅና በውሳኔውም ደስተኛ ሆኖ መቀበል ናቸው።
ምክኒያቱም እነሱ የአሏህን ጌትነት ፣ ኢስላም እውነተኛ ሃይማኖት መሆኑን እና ሙሐመድን {ሰ.ዐ.ወ} ነብይ መሆናቸውን ወደው ተቀብለዋልና።

Share