መግቢያ
በህይወት ጉዞ ላይ ሐዘን እና ድብርት እንደ ጥላ ሲከተሉን የሚሰማን ጊዜያት አሉ። ልባችን በሀሳብ ይከብዳ ል ፣ ተስፋም የራቀ ይመስላል። ነገር ግን ኢስላም ለዚህ ስሜት መለኮታዊ መድኃኒት እና ተግባራዊ መፍትሔዎችን ያቀርባል። ሐዘንን በኢስላም ማሸነፍ የጽናትና የእምነት ጥያቄ እንጂ የማይቻል ጉዳይ አይደለም።
ይህ ጽሑፍ የዚህችን ጠፊ አለም ተፈጥሮ በመገንዘብ ፣ ልብን በአላህ ዚክር በማረጋጋትና በአላህ ውሳኔ (ቀደር) ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር እንዴት ዘላቂ የልብ እርጋታን ማግኘት እንደሚቻል ይመራዎታል።
ከሀዘን እስራት ተላቀው ወደ ሰላም የሚወስደውን መንገድ አብረን እንመርምር።
የዚህ አለም እና የመጭው አለም እውነታ
የሐዘንን ስሜት ለማሸነፍ የመጀመሪያው እርምጃ የምንኖርባትን አለም (ዱንያ) ተፈጥሮ መገንዘብ ነው። በዚች ጠፊ አለም ውስጥ ምንም ነገር ቋሚ ሆኖ የሚዘልቅ ነገር የለም።
ህመምም ፣ ሐዘንም ፣ ችግርም ፣ በሽታም አይቀጥልም። በዚህ አለም ውስጥ ሁሉም ነገር ይጠፋል። እውነተኛውና ዘላለማዊው ህይወት ያለው ከሞት በኋላ ነው።
በቅርቡም ከሁለቱ ቡድኖች በአንደኛው ውስጥ ትሆናለህ፤ አንደኛው ቡድን በማያልቀው ዘላለማዊ ደስታና እርጋታ ውስጥ ሲሆን ሌላኛው ቡድን ደግሞ በዘላለማዊ ሥቃይና ፀፀት ውስጥ ይሆናል።
በአዕምሮህ ውስጥ ይህ ምስል ስታስቀምጥ የዚህ አለም ችግሮችና ህመሞች ሁሉ እንደ ቅንጣጢት (እንደ ብኛኝ) ያንሳሉ።
የሐዘን ምንጭ እና መለኮታዊው መድኃኒት
ሐዘንን በኢስላም ማሸነፍ ከመምትችልባቸው መንገዶች አንዱ በሕይወትህ ውስጥ ያለውን ትርፍ ጊዜ ለማስወገድ ራስህን በበጎ ሥራዎች መጥመድ ነው።
ሃያሉ አሏህን ማውሳት አብዛ። ጊዜ ሲኖርህ አእምሮህ በሀሳብ ይባክናል፤ ነገርግን ጠቃሚ በሆነ ስራ ስትጠመድ ለሐዘን ቦታ አይኖርህም።
ሐዘን ከሰይጣን መሆኑን አስታውስ፤ እሱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንድትሆን እንጅ መልካምን ነገር እንደማይሻልህ እወቅ፡፡
ይልቁንም በሕይወትህ ውስጥ ከሚጠቅምህ ነገር ሊያዘናጋህ ይፈልጋል። ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው?
ዚክር ፡ አላህን ማስታወስ
ጌታችን አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፦
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ረዕድ፡ 28)
“አዋጅ! አሏህን በማውሳት ልቦች ይረጋሉ”
አላህን ማውሳት (ዚክር) ለደከመው ልብ እንደ ንጹሕ አየር ፣ ለተጨነቀች ነፍስ ደግሞ እንደ ቀዝቃዛ ውሃ ነው። ልብህን በዚክር ስታረጥበው የሐዘን እሾኾች ይደርቃሉ።
በአላህ ውሳኔ (ቀደር) ውስጥ ያለ ጥበብ
ሃያሉ አሏህ ልብህን ለእስልምና አስፍቶልሃል። ሐዘንና ድብርት በህይወትህ ላይ እንዲሰለጥኑ እድል የማይሰጡ መሳሪያዎችንም ሰጥቶሃል። ለሚያጋጥምህ እያንዳንዱ ጉዳይ ከበስተጀርባው የአሏህ ጥበብና ውሳኔ አለ።
ለሚያጋጥምህ ችግር እና መሰናክል ሁሉ አሏህ ዘንድ ምንዳ አለህ፡፡ ፀጋዎቹን ሁሉ ስታመስግን ምንዳው እንደ ዝናብ ይጎርፋል።
ዛሬን ኑር ፡ የነብዩ (ﷺ) ወርቃማ ምክር
ሐዘን በአብዛኛው የሚመነጨው ያለፈውን በመጸጸት ወይም ስለወደፊቱ በመስጋት ነው። ነብያችን (ﷺ) ይህንን በሽታ በሚከተለው ወርቃማ ምክራቸው ፈውሰውታል፦
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
“ካነጋህ እስኪመሽ አትጠብቅ፤ ካመሸህ ደግሞ እስኪነጋ አትጠብቅ”
ይህን አስታውስ። የዘወትር ማስታወሻህም ላይ አስፍረው፡፡ ሐዘንህ እና ድብርትህ ከተፈጠረው ነገር ምንም የሚለውጡት ነገር የለም።
ያጣኸውን ነገር አያመጡልህም። ከሃያሉ አሏህ ውሳኔም ምንም ነገር አይለውጡም። ስለዚህ በጸጸት ከመኖር ተቆጠብ።
በአላህ ላይ መልካም እሳቤ አስብ
ከፊት ለፊትህ የምትመኘው መልካም ነገር አለና መጨውን በበጎ ተመልከት፤ መልካሙ ነገር ተስፋ አድርግ። በጌታህ ላይ ያለህን እሳቤ አሳምር። አላህ (ሱ.ወ) ሐዲሰል ቁድሲ ላይ እንዲህ ይላል፦
“እኔ ባሪያዬ እንደሚያስበኝ ነኝ፤ እንደፈለገም ያስበኝ”
ስለዚህ ሁሌም ከአላህ መልካምን ነገር ጠብቅ። ጉዳይህ ሁሉ በእርሱ እጅ ነው፤ እሱ ደግሞ ከአንተ እናት በላይ ለአንተ አዛኝ ነው።
ይህንን እውነት የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) እንዲህ በማለት አጽንተውታል፦
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ትርሚዚ)
“እወቅ! ሰዎች አንተን በአንድ ነገር ሊጠቅሙህ ቢሰባሰቡ እንኳ አሏህ ለአንተ ከፃፈልህ ነገር ውጪ ምንም ሊጠቅሙህ አይችሉም። አንተን በአንድ ነገር ሊጎዱህ ቢሰባሰቡ እንኳ አሏህ በአንተ ላይ ከፃፈው ነገር ውጪ ምንም ሊጎዱህ አይችሉም። ብዕሮቹ ተነስተዋል፤ መዝገቦቹም ደርቀዋል።”
ማጠቃለያ
ሐዘንን በኢስላም ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው? ሐዘን በእምነት ፣ በዚክርና በትክክለኛ አመለካከት ሊታከምና ሊሸነፍ የሚችል ጊዜያዊ ስሜት ነው።
ዱንያን በመረዳት ፣ ልብን በአላህ በማረጋጋት ፣ በቀደር በማመንና የዛሬን ህይወት ብቻ በመኖር እውነተኛ ሰላምን እናገኛለን።
ያለፈው አልፏል ፣ ወደፊት የሚመጣውም በአላህ እጅ ነው፤ የእኛ ድርሻ ዛሬን በኢማን መኖር ነው። ሐዘን ሲሰማህ ወደ አላህ ሽሽ፤ እሱ ከሁሉም ነገር በላይ ለአንተ ቅርብ ነውና።
እርስዎ ሐዘን ሲሰማዎት ከእነዚህ ምክሮች ውስጥ የትኛውን በብዛት ይጠቀማሉ? ጠቃሚ ሆነው ያገኙትን ዘዴ ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ላይ በማካፈል ሌሎችንም ይጥቀሙ።
Share