መግቢያ
በሰውነታችን ውስጥ ከሚመታው ልባችን በላይ ውድና ጥንቃቄ የሚሻ ንብረት የለንም። እሱ የህይወታችን ምንጭ ብቻ ሳይሆን የፈጣሪያችን እይታ ማረፊያና የኢማናችን ማዕከል ነው። በመሆኑም የልብ እንክብካቤ በኢስላም ተራ የጤና ጉዳይ ሳይሆን የህልውናችን መሰረት ነው።
ይህ ውድ አካል መንፈሳዊ ገጽታ ያለው ሲሆን በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሊደክም ፣ ሊቆሽሽና ሊታመም ይችላል።
ይህ ጽሑፍ የልብን ታላቅ ደረጃ ፣ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ እና ከሁሉም በላይ ልባችን ንጹሕ ፣ ህያውና ከፈጣሪው ጋር የተገናኘ ለማድረግ የሚረዱንን ኢስላማዊ መንገዶች በጥልቀት ይዳስሳል።
የልብ ታላቅ ደረጃ
ልብ (ቀልብ) በኢስላም በደረት ውስጥ ያለች ስጋ ብቻ አይደለችም። እሷ የመላው ሰውነታችን ንጉስ ናት። ልብህ የሰውነትህ ንጉስና የፈጣሪህ እይታ ማረፊያ ነው።
መለኮታዊ ተአምርና ምልክት ነው። በህይወት ውስጥ ሆኖ ይመታል፤ ይህን የተሰጠህን ፀጋ ግን ላታስተውለው ትችላለህ።
የአላህ (ሱ.ወ) እይታ የሚያርፈው በውጫዊ ገጽታችን ላይ ሳይሆን በልባችን እና በስራችን ላይ ነው። ይህች ልብ ከተስተካከለች ፣ መላው ህይወታችን ይቃናል፤ እሷ ከተበላሸች ደግሞ ሁሉም ነገር ይበላሻል።
የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ሲያረጋግጡ እንዲህ ብለዋል፦
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪና ሙስሊም)
‹‹ንቁ! በሰውነት ውስጥ አንዲት ቁራጭ ሥጋ አለች። እሷ ከተስተካከለች መላው ሰውነት ይስተካከላል፤ እሷ ከተበላሸች ደግሞ መላው ሰውነት ይበላሻል። እርሷም ልብ ናት።››
የልብ እንክብካቤ ለምን ያስፈልጋል?
ውድ ንብረቶችህን ከጉዳት እንደምትጠብቅ ሁሉ ልብህንም ጠብቃት (ተንከባከባት)። ልብህን ከሚያጠቃ ማንኛውም በሽታ ልትጠብቅ ይገባል። ልብሶችህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚቆሽሹና ማፅዳት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ልብህንም እንደዚያው ማፅዳት ያስፈልጋል።
ልብህን ጥላሸት ቀሚቀባ ነገር ሁሉ ማንፃት ያስፈጋል። ኮምፒውተርህን በፕሮግራሞችና በማዘመኛዎች እንደምትንከባከበው ሁሉ ልብህም እንደዚያው እንክብካቤህን ትፈልጋለች። የላቀ ዓላማውን ታስታውስ ዘንድ ልዩ እንክብካቤህን ይሻል፡፡
ስለዚህ ይህንን ውድ አካል አሏህን ከማውሳት አትከልክለው። የሚገባውን ምግብ እና የሚገባውን እረፍት አትንፈገው።
ልብን የሚያጠቁ መንፈሳዊ በሽታዎች
ልብ የአካላችን ክፍል እንደመሆኑ በመንፈሳዊ በሽታዎች ይታመማል። በሽታዎቹ በአይን የማይታዩ ስውር ገዳዮች ናቸው። ከእነዚህም መካከል፡-
- ኩራት (ኪብር)፡ ራስን ከሌሎች አብልጦ ማየትና እውነትን አለመቀበል።
- ምቀኝነት (ሀሰድ)፡ ሌሎች ያገኙት ጸጋ እንዲወገድላቸው መመኘት።
- ይዩልኝ (ሪያእ)፡ አምልኮን ለሰዎች እይታ ብሎ መስራት።
- ዝንጋቴ ፡ አላህን ፣ አኼራን እና የህይወትን አላማ መዘንጋት።
የልብ መድኃኒቶች ፡ ቀልብን የማፅጃና የማለምለሚያ መንገዶች
ልባችንን ከነዚህ በሽታዎች ለማንጻትና ለማለምለም ኢስላም ድንቅ መድኃኒቶችን አዟል።
ይህንን ውድ አካል ከምግቡ አትከልክለው። የልብ ዋና ምግቡና እርጋታው አላህን ማውሳት (ዚክር) ነው።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ረዕድ 13፡28)
“አዋጅ! አሏህን በማውሳት ልቦች ይረጋጋሉ።”
ዚክር (አሏህን ማውሳት) የዕለት ተዕለት ህይወትህ አካል አድርግ።
- ሶደቃ (ምጽዋት) እና ሰለዋት
ልብህ እንዲለሰልስ ሶደቃ (ምፅዋት) ስጥ። በአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ ሰለዋት ማውረድን አብዛ። እሳቸው አንተን ለመገናኘት በናፍቆት ዓይኖቻቸው እንባ ያነቡ ናቸውና። ምንምእንኳ ዓይንህ ባያያቸውም በነብይነታቸው ላይ ምስክር ሁን።
- ቁርአን፡ የልቦች ጸደይ
ቁርአን ለደረቀች ልብ እንደ ዝናብ ፣ ለጨለመች ልብ እንደ ብርሃን ነው። እሱን ማንበብ ፣ ትርጉሞቹን በጥልቀት ማስተንተን እና አስተምህሮቶቹን በህይወት ላይ ተግባራዊ ማድረግ ለልብ ከሁሉ የተሻለ መለምለሚያ መድሃኒት ነው።
ሞት የማይቀር እውነት መሆኑንና ከፊታችን ዘላለማዊ ህይወት እንዳለ ማሰብ፣ ልብን ከዱንያ ዝንጋቴ ያነቃዋል።
ሞት የማይቀር እውነት መሆኑን አስታውስ። ዘላለማዊውን ህይወት አስታውስ፡፡ ህይወትህ ፍፃሜ እንዲያገኝበት የምትፈልገውን ስራ ስራ።
ማጠቃለያ
የልብ እንክብካቤ የአንድ ጊዜ ስራ ሳይሆን የህይወት ዘመን ጉዞ ነው። ልክ ሰውነታችን በየቀኑ ምግብ እንደሚያስፈልገው ፣ ልባችንም በየቀኑ መንፈሳዊ ምግብና ጽዳት ያስፈልገዋል።
ንጹሕ ልብ ይዞ ወደ አላህ መመለስ የመጨረሻው ስኬት ነው። ስለዚህ ዛሬውኑ ልባችንን በዚክር ፣ በቁርአን እና በመልካም ስራዎች እንንከባከብ።
ልብዎን ለማጥራት በዕለት ተዕለት ህይወትዎ ውስጥ የሚተገብሩት የትኛውን ተግባር ነው? የእርስዎን ተሞክሮ ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ላይ በማካፈል ሌሎችን ያነቃቁ።
Share