የትምህርቱ አጭር መግለጫ
በሞተ ሰው ማዘን እና መፅናናት እና መቃብሩን ሄዶ ማየት ጋር የተያያዙ አንድ ሙስሊም ሰው ሊከተላቸው የሚገቡ አህካሞች እና ስነ-ስርአቶች አሉ፡፡ በዚህ ትምህርት ውስጥ ስለ ተወሰኑት ትማራላችሁ፡፡
የትምህርቱ አላማ
የሟቹን ሰው ቤተሰቦች እና ዘመዶች ማፅናናት እና መቃብሩን ሄዶ ማየት ጋር የተያያዙ አህካሞችን እና ስነ-ስርአቶችን ትማራላችሁ፡፡
ማፅናናት
የሟቹን ሰው ቤተሰቦች ማፅናናት የተወደደ ነው፡፡ በመልካም ንግግር ከደረሰባቸው ነገር እንዲበረቱ ማድረግ ፣ ለሟቹ ሰው ዱአ ማድረግ ፣ ቤተሰቦቹን እና ዘመዶቹን ማበረታታት እና እንዲታገሱ ማድረግ የተወደደ ነው፡፡
እንዲሁም ከአሏህ ምንዳ እንዲፈልጉ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ 1284 ፣ ሙስሊም 923)
‹‹አሏህ የሚወስደው ማንኛውም ነገር የእሱ ነው፡፡ እሱ የሰጠው ማንኛውም ነገር የእሱ ነው፡ በዚህ አለም ውስጥ ከእሱ የሆነ ማንኛውም ነገር በጊዜ የተገደበ ነው፡፡ እናም ታገሱ፤ የአሏህን ምንዳ (ሽልማት) ተስፋ አድርጉ፡፡
የሟቹ ቤተሰቦች እና ዘመዶች ከቀብር በፊትም ሆነ በኋላ በማንኛውም ቦታ ማለትም መስጅድ ውስጥ ፣ የመቃብር ቦታ ፣ ቤት ፣ የስራ ቦታ ወ.ዘ.ተ ማፅናናት ይቻላል፡፡
የሃዘን መግለጫ ድንኳን በመትከል ወይም የእራት ግብዣ በማድረግ እና ለእነዚህ አላማ መሰባሰባቸው በጣም መጋነን የለበትም፡፡ ምክኒያቱም የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እና የእነዚያ እንቁ ሶሃቦች ሱና አይደለምና፡፡
ለሟቹ ሰው ማዘን እና ማልቀስ
ማልቀስ ተፈጥሯዊ እዝነት እና የማጣት እና የሐዘን ስሜት መግለጫ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ልጃቸው ኢብራሂም ሲሞት እንባቸውን አፍሰዋል፡፡ (ቡኻሪ 1303 ፣ ሙስሊም 2315)
በሞተው ሰው ማዘን እና ማልቀስ በተመለከተ እስልምና ህገ ደንቦችን አስቀምጧል
- ከመጠን በላይ እና ድምፅ ከፍ አድርጎ ማልቀስ እንዲሁም ከእስልምና ህግጋት ጋር የሚጣረሱ ድርጊቶችን መፈፀም ለምሳሌ ፀጉርን መላጨት ፣ ደረት መምታት ፣ ፊትን መንጨት ወ.ዘ.ተ እስልምና ከልክሏል፡፡
- አንዲት ሴት የሞተባት ባሏ ካልሆነ በቀር ከዘመዶቿ አንዱ በመሞቱ ምክኒያት ጌጧን መተው አይፈቀድላትም፡፡
- የሚስት ሐዘን፡ ባሏ የሞተባት ሴት በመጠበቂያዋ ጊዜ (በኢዳዋ) የተወሰነ ነገሮችን ማክበር እና መጠበቅ አለባት፡፡
ባሏ የሞተባት ሴት የመጠበቂያ ጊዜ
ይህም አራት ወራት ከአስር ቀን ወይም ነፍሰጡር ከሆነች ደግሞ አስክትወልድ ድረስ ነው፡፡
ባሏ የሞተባት ሴት በመጠበቂያ ጊዜዋ ምን ማድረግ አለባት
- ሽቶ መቀባት ፣ ጌጣ ጌጥ መልበስ ፣ ሜካፕ ፣ ሂና መቀባት ሁሉንም አይነት ኮስሞቲክስ መጠቀም የለባትም፡፡
- ማንኛውም አይነት ቀለም እና ቅርፅ ያላቸውን የተለመዱ ልብሶችን መልበስ ይፈቀድለታል፤ የመዋቢያ እና የማጌጫ አስካልሆነ ድረስ፡፡ ገላዋን ከመታጠብ ፣ ፀጉሯን ከማበጠር አትከከለከልም፡፡ ባስፈለገ ጊዜ ማታ ሳይሆን ቀን ላይ ከቤት ወጥታ መሄድ ትችላለች፡፡ ያለ ጥርጣሬ የማታቃቸውንም ወንዶች ማናገር ትችላለች፡፡
መቃብርን መጎብኘት፡ መቃብርን መጎብኘት በሶስት ይከፈላል፡፡
- የተወደደ ጉብኝት
- የተፈቀደ ጉብኝት
- የተከለከለ ጉብኝት
1 የተወደደ ጉብኝት
ይህ አይነቱ ጉብኝት (ዚያራ) ሞት እና መጭው አለም ለማስታወስ ተብሎ የሚደረግ ዚያራ ነው፡፡ የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም 977 ፣ ትርሚዚ 1054)
‹‹መቃብርን መጎብኘት እከለክላችሁ ነበር፡፡ (አሁን ግን) ጎብኟቸው፡፡›› በሌላ ሐዲስ ደግሞ ‹‹የመጭውን አለም ህይወት ያስታውሳችኋል›› ተብሏል፡፡
መቃብሮችን መዘየር በዚያኑ ሐገር ውስጥ ሆኖ ረዥም ጎዞ ከሌለው እና እንደ አምልኮ ተግባር የማይቆጠር ከሆነ ነው፡፡
2 የተፈቀደ ጉብኝት
ሞትን ለማስታወስ ተብሎ ሳይሆን ለሌላ ለተፈቀደ አላማ ተብሎ የሚደረግ ጉብኝት ነው፡፡ ሆኖም የተከለከለ ነገርን አያካትትም፡፡ ለምሳሌ የመጭውን አለም ህይወት ለማስታወስ ሳያስቡ የዘመዶችን ወይም የጓደኞችን መቃብር መዘየር፡፡
3 የተከለከለ ጉብኝት
ይህ የቀብር ዚያራ የተከለከለ ነገር የታከለበት ነው፡፡ ለምሳሌ በመቃብር ላይ መቀመጥ ፣ በእሱ ላይ መረማመድ ፣ ደረት መደሰቅ እና ድምጥፅን ከፍ አደርጎ ማልቀስ ወይም የፈጠራ (የቢድአ) ስራዎች ለምሳሌ የሞተን ሰው መለመን (መማፀን) ፣ ከእሱ በረከትን መፈለግ ወይም የሽርክ ተግባራት ለምሳሌ ከሞተው ሰው ፍላጎትን እንደያሟላለት እና እንዲረዳው መለመን ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡
የሙስሊም ሰው የቀብር ጉብኝት ከጀርባው ብዙ አላማዎች ሊኖተኖሩት ይገባል፡፡
- የመጭውን አለም ህይወት ማስታወስ ፣ ከሞት እውነታ ተግሳፅ ለማግኘት እና ጥንቃቄ ለማድረግ፡፡
- ለሟቹ ሰው እዝነት እና ምህረትን በመለመን ለእሱ ደግነትን ለማሳየት፡፡ ምክኒያቱም ይህ ሟቹ ሰው በመጎብኘታቸው እና ስጦታ ለእነሱ በመስጠታቸው ይደሰታሉና ነው፡፡
- መቃብርን የሚጎበኘው ሰው የነብዩ ሱና በመከተል መቃብሮችን በመጎብኘቱ እና ምንዳ በማግኘቱ ለእራሱ ደግነትን ያሳያል፡፡
መቃብሮችን በሚጎበኝበት ጊዜ ለሞተው ሰው አክብሮት ሲባል በመቃብሩ ላይ ከመቀመጥም ሆነ ከመረማመድ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይህን አስመልክቶ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም 971)
‹‹አንዳችሁ መቃብሩ ላይ ልብሱን የሚያቃጥል ፣ ቆዳው ጋር ከሚገናኝ ፍም የከሰል ድንጋይ ላይ ቢቀመጠጥ ይሻለዋል፡፡››
መካነ መቃብር አካባቢ ላይ ዱአ ማድረግ
መካነ መቃብርን በሚጎበኙ ጊዜ ከሚደረጉ ዱአዎች መካከል፡
‹‹በዚህ መኖሪያ የምትኖሩ አማኞች ሰላም በእናንተ ላይ ይሁን፡፡ አሏህ ከፈቀደ እኛም እንቀላቀላችኋለን፡፡ አሏህ ከመካከላችን ለተቀደሙትም ወደ ኋላ ለቀሩትም ምህረት ይለግሳቸው፡፡ ለእኛም ለእናንተም ከአሏህ ዘንድ ደህንነትን እጠይቃለሁ፡፡›› (ሙስሊም 974)
‹‹በዚህ የሙዕሚኖች እና በሙስሊሞች መኖሪያ ያላችሁ ነዋሪዎች ሰላም በእናንተ ላይ ይሁን፡፡ አሏህ ከሻ እኛም እንከተላችኋለን፡፡ ለእኛም ለእናንተም ደህንነትን ከአሏህ እለምናለሁ፡፡›› (ሙስሊም 975)


Share