አላህን ማመስገን ፡ የተዘነጉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፀጋዎች ማስታወስ

Author picture
በዙሪያችን ያሉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የአላህ ፀጋዎች ቆጥረን እንዘልቃለን? እስኪ ቆም ብለን እናስተውል እና ከአመስጋኞቹ እንሁን!

መግቢያ

በየዕለቱ በምንኖርበት የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ቆም ብለን በዙሪያችን ያሉትን የአላህ ፀጋዎች ምን ያህል ጊዜ እናስተውላለን? አላህን ማመስገን የእምነታችን መሰረት ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ እንደ ቀላል የምንወስዳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶች አሉ።

ይህ ጽሑፍ አይናችንን እንድንከፍት ፣ ልባችንን እንድናነቃ እና በህይወታችን ውስጥ የተዘነጉትን ታላላቅ ፀጋዎች እንድናስታውስ ይጋብዘናል።

ከጤና እስከ ቤተሰብ ፣ ከትንፋሽ እስከ ስሜት ህዋሳት ድረስ ያለውን የጌታችንን ልግስና በማስተዋል ፣ “ከአመስጋኞቹ ባሮች” ለመሆን እንድንተጋ ያነሳሳናል። እስኪ ለአፍታ ከማማረር ወጥተን በፀጋዎቹ ላይ እናተኩር።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ነህል፡ 18)

‹‹የአሏህን ፀጋ ብትቆጥሩ አትዘልቁትም። በእርግጥ አሏህ አዛኝ መሃሪ ነውና።››

እንደ ቀላል የምንመለከታቸው የጤና ፀጋዎች

ህይወታችን የተገነባባቸው ነገር ግን ብዙ ጊዜ ትኩረት የማንሰጣቸው መሰረታዊ የአላህ በረከቶች አሉ። እስኪ ራስዎን እነዚህን ጥያቄዎች ይጠይቁ፡

  •  የማየት ፀጋ፡ አይንህን ብታጣ ኑሮህ ምን ሊመስል እንደሚችል አስበህ ታውቃለህን?
  •  የመስማት ፀጋ፡ የመስማት ችሎታህን ብታጣ የምትወዳቸውን ድምፆች ሳትሰማ መኖር ምን ያህል ከባድ ይሆን?
  •  የመንቀሳቀስ ፀጋ፡ እግሮችህን ድንገት ብታጣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ምን ያህል ይለወጥ ነበር?

በእነዚህ በምትዋኝባቸው የአላህ ፀጋዎች ውስጥ ያለውን የተሟላ ህይወትህን ምን ያህል ጊዜ ታስተውለዋለህ?

ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነቃ ፣ በዚያችው ሌሊት ከእንቅልፋቸው ያልተመለሱ ምን ያህል ሰዎች እንዳሉ አስበህ ታውቃለህ?

የህይወትና የደህንነት በረከቶች

ጤናና ደህንነት በገንዘብ የማይተመኑ ታላላቅ የአላህ ስጦታዎች ናቸው።

  •  የተራበ እንዳለ እያሰብክ በልተህ ታውቃለህ?
  •  ደህና መሆንህን የሚያረጋግጥ የህክምና ውጤት ስትቀበል፣ ይህ በራሱ ምን ያህል ታላቅ ፀጋ እንደሆነ አስተውለሃል?
  •  በዚያችው እለት በዓለም ዙሪያ ምን ያህል ሰዎች የህይወታቸው ፍፃሜ መቃረቡን የሚገልጽ መርዶ እንደሚሰሙስ ታውቃለህ?

በዙሪያችን ያሉ ፀጋዎች

ህይወትን ውብና አስደሳች የሚያደርጉ ነገር ግን ብዙ ጊዜ የማናስተውላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፀጋዎች አሉ።

  •  በዙሪያህ ያሉትን መልካም መዓዛዎች ስትተነፍስ፣
  •  ውብ የሆኑ ድምፆችን ስትሰማ፣
  •  ለሚወጣውና ለሚገባው እያንዳንዱ እስትንፋስህ፣
  •  የምትወዳቸውን ሰዎች በእጆችህ ስለመዳሰስህስ፣

ለእነዚህ ሁሉ ፀጋ ጌታህን ከልብህ አመስግነህ ታውቃለህ? አስብና አመስገግን!

የምንወዳቸው ሰዎች እና ማህበራዊ ህይወት

አላህ በዙሪያችን ስላደረጋቸው ውድ ሰዎች አስበህ ታውቃለህ? ወላጆችህ ፣ ልጆችህ ፣ የህይወት አጋርህና ወዳጆችህ መኖራቸው በራሱ ታላቅ ፀጋ መሆኑን አስተውለሃል? ያለነሱ ህይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል አስበኸዋል?

ከጥቃቅን ምኞቶችህ አንዱን ለማግኘት ስትል የማየት ፣ የመስማት ፣ የመዳሰስ ወይም ከእነዚህ ውድ ሰዎች አንዱን ትለውጥ ነበር?

ከማማረር ወደ አላህን ማመስገን የምናደርገው ጉዞ

እንግዲህ ይህን ሁሉ የአላህ ፀጋ እያየህና እያሰብክ ፣ አሁንም የሌሉህን ጥቂት ነገሮች እያሰብክ ማማረርና መበሳጨትን ትቀጥላለህ? የአላህ ፀጋዎች ለመቁጠር እስኪያቅትህ ድረስ የበዙ መሆናቸውን መቼ ነው የምትገነዘበው?

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ረህማን)

“የትኛውን የጌታችሁን ፀጋዎች ታስተባብላላችሁ?”

እጆችህን ወደ ሰማይ የምታነሳበት ፣ በሩኩዕ ዝቅ የምትልበት እና ለሰማያትና ለምድር ፈጣሪ ምስጋናን እያቀረብክ በግንባርህ ተደፍተህ ሱጁድ የምታደርግበት ጊዜ አልደረሰም?

ብዙዎች ያጧቸውን እነዚህን ታላላቅ ፀጋዎችና በረከቶች አንተ ተችረሃል… እናም “ከአመስጋኞቹ” የምትሆንበት ጊዜ አሁን አይደለም?

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ሰበእ፡ 13)

“ከባሮቼም አመስጋኞች ጥቂቶቹ ናቸው።”

ማጠቃለያ

የአላህ ፀጋዎች እንደ ውቅያኖስ የጠለቁና እንደ ሰማይ የሰፉ ናቸው፤ ቆጥረን አንዘልቃቸውም። እውነተኛ ደስታና እርካታ ያለው የሌለንን በማሰብ በማማረር ሳይሆን ፣ ያለንን በማስተዋልና አላህን ማመስገን ላይ ነው።

በየዕለቱ ቆም ብለን እነዚህን በረከቶች እናስተውል፤ በሰላት ፣ በዚክርና በዱዓ ምስጋናችንን እንግለፅ። ይህን በማድረግ ከጥቂቶቹ አመስጋኝ ባሮች መካከል ለመሆን እንችላለን።

እርስዎ በህይወትዎ ውስጥ በብዛት ሊያመሰግኑበት የሚገባው የተለየ ፀጋ ምንድን ነው? ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ላይ ያጋሩን።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share