ችግረኛ በለመነ ጊዜ መልስ የሚሰጠው ማነው?

Author picture
ችግረኛ በጠራ ጊዜ መልስ የሚሰጠው አሏህ ብቻ ነው። በመከራ ፣ በሀዘንና በችግር ጊዜ ወደ እርሱ በመቃረብና እሱን በመለመን እንዴት እፎይታና ሰላም ማግኘት እንደሚችሉ በዚህ ጽሁፍ ይረዱ።
ችግረኛ በለመነ ጊዜ መልስ የሚሰጠው
  • ችግረኛ በለመነ ጊዜ መልስ የሚሰጠው ማነው?
  • ችግረኞች አቤቱታቸውን የሚያቀርቡለት አካል ማነው?
  • መከራ የደረሰባቸው ፍጡራን ሁሉ የሚመኩበት ፣ የሚጠጉበት እና የሚጠይቁት ምላሶች አዘውትረው የሚያዎሱት እና ልቦች የሚያመልኩት ማንን ነው?

እሱ አሏህ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም። በችግርና በደስታም ጊዜ እሱን የመማፀን ፣ በመከራ ጊዜያትም ወደ እሱ የመቃረብ እና በደጃፉ ላይ ድፍት ብለን እያለቀስን ከወንጀሎቻችን መሃርታን እየጠየቅን እሱን የመለመን ሐቅም አለብን።

የዚያኔ ችሮታው ይመጣል ፣ እርዳታውም ይደርሳል ፣ መድህኑም በፍጥነት ይገኛል።

አል-ቁርአን

{ሱረቱ ነምል 27:62}

«ችግረኛ በለመነው ጊዜ መልስ የሚሰጥ ከአሏህ ሌላ ማን አለ?»

ሊሰምጥ የነበረውን ያድናል፤ የጠፋውን ይመልሳል፤ የተፈተነውን ይደርስለታል፤ የተበደለውን ይረዳል፤ የጠመመውን ያቃናል፤ የታመመውንም ያሽራል፤ መከራ የደረሰበትን መከራውን ያነሳለታል።

አል-ቁርአን

{ሱረቱል አነከቡት 29:65}

«በመርከቦች ውስጥ በተሳፈሩ ጊዜ አሏህን መገዛትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ሲሆኑ ይጠሩታል።»

አሁን የሃዘን ፣ የጭንቅ ፣ የትካዜና የችግር ማላቀቂያ ዱአዎችን ፀሎቶችን አልዘረዘርልህም። ባይሆን ከሱ ጋር መልካም ንግግርን ታውቅ ዘንድ አውቀህም ትጠራው ፣ ትለምነውና ትማፀነው ዘንድ የሱና መጽሐፍት እጠቁምሃለሁ።

እሱን ካገኘህ ሁሉን ነገር አግኝተሃል። በሱ ኢማን ፅኑ እምነትን ካጣህ ደግሞ ሁሉን ነገር አጥተሃል።

ጌታህን መለመንህ እራሱን የቻለ አምልኮ ነው። የምታጣውን ከማግኘትህም የበለጠ የመታዘዝ ምልክት ነው።

አሳምሮ የዱዓእ አደራረግ ዘዴን የሚያውቅ ሰው ባይተክዝ ባይጨነቅ እና ባይቸገርም ይገባዋል።

የእሱ የአሏህ ገመድ ሲቀር ሁሉም ገመዶች ይቆረጣሉ። ሁሉም በሮችም ይዘጋሉ የሱ በር ሲቀር። እሱም ቅርብ ፣ ሰሚ ፣ መልስ ሰጭ ሲሆን ችግረኛ በጠራው ጊዜ መልስ ይሰጣል።

አንተ ድሃ ፣ ደካማና ችግረኛ ስትሆን እሱ ደግሞ ባለሃብት ፣ ሃያልና ብቸኛ እንዲሁም ሁሉን ቻይ በመሆኑ ትለምነው ዘንድ ያዝሃል።

አል-ቁርአን

{ሱረቱል ጋፊር 40:60}

«ጌታችሁም አለ ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና።»

መከራዎች ቢደርሱብህ እና ችግሮች ቢያጋጥሙህ እሱን አብዝተህ አውሳው። የነፃነት ዘውድን ታገኛለህና ስሙን በመቀደስ በግንባርህ ተደፋ።

ተዋረድለት እሱን በማምለክ የመድህን ኒሻን ትሸለማለህ።

እጅህን ዘርጋ፤ መዳፎችህን ከፍ አድርግ ፤ አብዝተህ ጠይቀው፤ ችክ ብለህ ለምነው፤ በሩን ተመላልሰህ አንኳኳ፤ እዝነቱን ተጠባበቅ፤ እርዳታውን ከጅል፤ ስሙን አውሳ፤ በሱ ያለህን እምነት አጠንክር፤ ወደ እሱ ተጠጋ ያለማቋረጥ ተገዛው ትድናለህ ትደሰታለህም።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share