የአንብብ ትውልድ ሆይ! የድልህን ብስራት አንብብ

Author picture
ሙስሊሞች በኡኹድ ጦርነት ተሸንፈው በእጃቸው የነበረውን ድል ተነጥቀው ፣ ሽንፈትን ተከናንበው አዝነውና ተክዘው በተመለሱ ጊዜ አሏህ ሙዕሚኖች ድል የሚያደርጉበትን መንገድ እንዲህ ሲልነበር ያመላከታቸው።
የአንብብ ትውልድ ሆይ! የድልህን ብስራት አንብብ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ሙስሊሞች በኡኹድ ጦርነት ተሸንፈው በእጃቸው የነበረውን ድል ተነጥቀው ፣ ሽንፈትን ተከናንበው አዝነውና ተክዘው በተመለሱ ጊዜ አሏህ ሙዕሚኖች ድል የሚያደርጉበትን መንገድ እንዲህ ሲልነበር ያመላከታቸው።

አሏሁ አዘወጀል በቅዱስ ቃሉ በሱረቱል ኢምራን አንቀፅ 139 ላይ እንዲህ ይላል፦

{139} ደካሞች አትሁኑ፤ አትዘኑም። በእርግጥ እውነተኛ አማኞች ከሆናችሁ የበላዮች (አሸናፊዎች) ትሆናላችሁ።

             {አል-ቁርአን 3:139}

ለምን ሶሃቦች (ረ.ዐ) አያዝኑ ፣ ለምንስ አይተክዙ ፣ ለምንስ አይደነግጡ? ምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ በላይ ምርጥ የሆኑ 70 ሶሃቦች ያኔ ተገለዋል፤ ብዙዎች ተጎድተዋል ቆስለዋልም።

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሳይቀሩ ፊታቸው በደም እስኪታጠብ ድረስ ቆስለዋል። በጭንቀት ላይ ሆነው ድክምክም እንዳሉ ጉንጮቻቸው ላይ ያለውን ደም እያበሱ በእርግጥ የመልዕክተኛውን ፊት በደም በለወሱት ሰዎች ላይ የአሏህ ቁጣ ብርቱና ከባድ ነው አሉ።

ነገርግን ይህ ሽንፈት ግዜያዊ መሰናክል ቢሆንም  ሙዕሚኖች የሽንፈታቸውን ምክኒያት እንዲመረምሩ አስችሏቸዋል። የጥቂት ሙዕሚኖች ስህተት እና ሃጢያት የሙሉ ወታደሮችን ድል አስነጥቋቸዋል።

በኸሊፋዎች ዘመን ሙስሊሞች በማንኛውም ነገር የላቁና የተከበሩ ነበሩ።

ታዲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እኛ ሙስሊሞች መጥፎ ነገሮችን እየሰራን እና እያስፋፋን በመምጣታችን ፣ በማናውቀው ነገር ፈትዋ ለመስጠት በመቻኮላችን ፣ ከእምነታችን በላይ ገንዘብን ፣ ሃብትን ፣ ስልጣንን በመውደዳችን ፣ ከሰዎች ዘንድ ዝናንና ክብርን በመፈለጋችን ፣ የልዩነትን በር በመክፈታችን ያን ክብርን እና ታላቅነት አጥተን ዛሬ የማንም መጫወቻ ሁነናል።

ዛሬ በእኛ ላይ በሚዘምቱ ኩፋሮች ላይ መዝመት ቀርቶ ሙስሊሞች በሙስሊሞች ላይ መዝመት ጀምረናል። የሙስሊም ሃገራት እንኳ ሳይቀሩ ለአምስቱ ሃያል አገራቶች አጎብዳጅ ሁነዋል።

  • በፓለስታይን ፣ በኢራቅ ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በፓኪስታን ፣ በከሽሚር ፣ በበርማ ፣ በሊብያ ፣ በሶርያ እና በየመን የሚገደሉት ንፁሃን መስሊሞች እንደው ምን አድርገው ይሆን?
  • የሰው ሃገር ወረው? በኩፋሮች ላይ በመዝመት ኩፋሮችን ጨፍጭፈው ነው? የሌሎች ሃገሮችን ድንበር ገፍተው ነው? ምን አድርገው ነው?
  • ሌሎች ሙስሊም ሃገራቶችስ እነዚህን ሃገራቶች የሚወሩና ሙስሊሞችን የሚጨፈጭፍትን ለመታገል ምን አደርጉ?
  • ምንም! የአቋም መግለጫ እንኳ አያወጡም! ታዲያ ሙዕተሲምን ምሳሌ አድርገው የሚከተሉ መሪዎች የታሉ?

ኡመር ኢብን ኸጧብ (ረ.ዐ) የሰአድ ቢን አቢወቃስ ወታደሮችን ወደ ቀድሲያ ጦርነት ሲልኩ ከጠላቶቻችሁ በላይ ወንጀላችሁ ለእናንተ አደገኛ ነውና ከጠላቶቻችሁ በላይ ወንጀላችሁን ፍሩ ብለው ነበር።

እኛ ሙስሊሞች በጠላቶቻችን ላይ አሸናፊዎች የምንሆነው ሃጢያታቸው ከእኛ ሃጢያት በላይ በበዛ ጊዜ እንጅ በሌላ በምንም ምክኒያት አይደለም።

ወንጀላችን ከጠላቶቻችን ወንጀል ጋር እኩል ከሆነ ያኔ በቁጥራቸው ብዛት ያሸንፉናል ሲሉ መከሩት።

ሰአድ (ረ.ዐ) ፐርዥያኖችን ለመዋጋት ሲነሳ የመሪውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ አስካሪ መጠጥ አዘውትሮ የሚጠጣውን ወታደሩን አቡ መህጃን (ረ.ዐ) ወደ ቤቱ ወስዶ አሰረው።

አቡ መህጃህ እንደታሰረው የሰአድን ሚስት ልቧን የነካትን የግጥም ስንኝ ቋጠረ። ይህንም ስትሰማ ልቧ አልችል ብሏት ወንድሞቹጋ ጦርሜዳ ሄዶ እንዲሳተፍ ብላ ከታሰረበት በመፍታት የሰአድን ፈረስ  አስይዛ ላከችው።

አቡ መህጃህ ጦርነቱን ተቀላቅሎ በሚገርም አኳኋን ተጋድሎ ከተመለሰ ብኋላ ተመልሶ ወደታሰረበት ይገባል። ሰአድ የዚህን ሰውየ ማንነት እስኪያውቅ ድረስ ለሶስት ቀን እንዲህ እያደረገ ቆየ።

ሰአድ (ረ.ዐ) አቡ መህጃህ እንደሆነ ባወቀ ጊዜ የታሰረበትን ነገር ከፈታለት ቡኋላ በአሏህ ይሁንብኝ! ከዚህ ብኋላ አስካሪ መጠጥ በመጠጣትህ አላስርህም አለው።

አቡ መህጃህም በአሏህ ይሁንብኝ! እኔም ከዚህ ብኋላ አስካሪ መጠጥ አልጠጣም ሲል መለሰለት። ወታደሮቹ ድልን ተጎናፅፈው፤ ሰልማኑል ፋሪስን (ረ.ዐ) የፐርዥያ አዲስ መሪ አድርገው ሹመው ተመለሱ።

ድል እና ሽንፈት ፣ ማግኘትና ማጣት ፣ ስኬትና ውድቀት በገንዘብ ፣ በሐብት ፣ በመሳሪያ ፣ በቁጥር ፣ በክህሎት አይወሰንም።

ይልቁንም እነዚህ ነገሮች የሚወሰኑት አሏህን በመታዘዝ እና ባለመታዘዝ ሚዛን ነው። በተናጠልም ይሁን በግሩፕ የበለጠ አሏህን ስንታዘዝ አሏህ የበለጠ ወደ ድል ደጃፍ ያቀርበናል።

አሏህ የበለጠ ባመፅን ቁጥር አሏህ ድልን ከእኛ ያርቅብናል። የአንድ ሙስሊም ወንጀል የብዙሃኖችን ድል ሊያዘገይ እንደሚችል እንወቅ። ጣታችነን ሌሎች ላይ ከመቀሰራችን በፊት እራሳችንን በደንብ እንመርምር!!!

ያ ኢኽወቲ ፊላህ! እስኪ ያለንበትን ሁኔታ እናስተውል! እራሳችነን እንፈትሽ! ሶላት የማንሰግድ ፣ ሲመቸን የምንሰግድ፤ ሲመቸን ደግሞ የምንተው ስንቶቻችን እንሆን?

ዘካ ለመስጠት የምንሰስት ፣ አስካሪ መጠጥ የምንጠጣ ፣ ሐራም ነገሮችን የምንሸጥ ፣ የከንፈር ወዳጅ ያለኒካህ ያበጀን ፣ የምንሰርቅ ፣ የምናጭበረብር ፣ ሃራም ነገሮችን የምንበላና የምንጠጣ ፣ ዝሙት የምንሰራ ፣ መስጊድ አካባቢ ችግረኞች ተቀምጠው ገንዘባችነን በፋሽንና በቅንጦት ነገሮች ላይ የምናባክን ስንቶቻችን እንሆን?

ሙስሊሞች ሲታሰሩ ፣ ከሐገር ሲባረሩ ፣ ሲገደሉ ታዲያ ለምን እጃችነን መቀሰር አቃተን። ለምን ውዷ ጊዜያችነን የማይረባ ነገር እያየን እና እየተጫወትንስ እንደቀልድ እናሳልፋለን ።

ዛሬ ላይ ለሙዚቃና ለፊልም ከምንሰጠው ሰአት በላይ ለቁርአን አንድ ደቂቃ መስጠት ከብዶናል።

ታዲያ ይህን ሁሉ እየሰራን የአሏህን ድል ከመጠበቅ ይልቅ የአሏህን ቁጣ እና ቅጣት መጠበቁ አይቀልም ትላላችሁ??

ወንጀሎችን በፈፀምን ቁጥር የሙስሊሞችን ድል እያዘገየን ነው። ከሃዲያኖች በዲናችን እንዲጫወቱ ፣ ቁርአንን እንዲያረክሱ ፣ ሙስሊሞች እንዲታሰሩና እንዲገደሉ ፣ የእህቶቻችን ክብር እንዲደፈር እየፈቀድን መሆኑን ልናውቅ ይገባል!!!

139 ደካሞች አትሁኑ፤ አትዘኑም። በእርግጥ እውነተኛ አማኞች ከሆናችሁ የበላዮች (አሸናፊዎች) ትሆናላችሁ።

               {አል-ቁርአን 3:139}

አሏህ  እረፍትን ፣ እርዳታን ፣ አሸናፊነትን ፣ የበላይነትን እና ድልን እንደሚያጎናፅፈን ቃል ገብቷል። መቼ? እውነተኛ አማኞች በሆን ጊዜ፤ እራሳችነን ለአሏህ ፍቃድ ሙሉ በሙሉ በማስገዛት በአሏህ መንገድ መታገል በጀመርን ጊዜ ነው!!!

For more free Islamic pamphlets, brochures and books delivery please subscribe to Youth Mission የወጣቱ ተልዕኮ

Related posts

ሸሃዳ የእምነት ምስክርነት ቃል

ሸሃዳ የእምነት ምስክርነት ቃል

ሸሃዳ ማለት የእምነት ምስክርነት ቃል ነው። ላኢላሃ ኢለሏህ (ከአሏህ ውጭ ሌላ አምላክ የለም) ማለት ከአሏህ ውጭ በሃቅ ሊያመልኩት የሚገባ ሌላ አምላክ የለም ማለት ነው።

Read More »
መልእክት ለሙስሊም ወጣቶች

መልእክት ለሙስሊም ወጣቶች፡ ሕይወትን በእስልምና ፣ በቁርአን እና በሱና መሰረት መኖር

ውድ ሙስሊም ወጣቶች! በዚህ ወሳኝ የሕይወት ምዕራፍ ላይ የምትገኙ ሙስሊም ወጣቶች ልባዊ ሰላምታችን እና ውዴታችን ይደረሳችሁ። ይህ ጊዜ የብርታት፣ የጉጉት፣ የእውቀት ፍለጋ እና ለወደፊት ህይወታችሁ

Read More »

Share