አዋጅ! አሏህን በማውሳት ልቦች ይረጋሉ! እውነተኛ መሆን አሏህ ዘንድ ተወዳጅ ምግባር ነው። ግልፅነትም የቀልብ ማፅጂያ ነው። ተሞክሮም ማስረጃ ነው።
መሪም ቤተሰቡን አይዋሽም። ልብን በማረጋጋትና የላቀ ምንዳን በማስገኘት ከዚክር (አሏህን ከማውሳት) የተሻለ ስራ አልተገኘም።
አል-ቁርአን
ሱረቱ ደህር 76:9
«አስታዉሱኝ አስታውሳችኋለሁና።»
ጥራት የተገባውን ጌታ ማውሳትም ምድራዊ ጀነት ሲሆን ያልገባት ሰው የአኺራውን ጀነት አይገባትም።
ነፍስንም ከሚፀናወቷት የድካም ፣ የጭንቀትና የመዛባት ስሜቶች ያላቅቃታል። እንዲያውም ወደ ስኬትና መድህን የሚመራ አቋራጭ መንገድ ነው።
አሏህን ማውሳት የሚያስገኛቸውን ፋይዳዎች ለመገንዘብ ሰማያዊውን ራዕይ (ቅዱስ ቁርአን) ያካተቱ መዛግብትን ማሰስ ትችላለህ። ፍቱን መድህንን ከሻህ ደግሞ ቀን ተሌት አጣጥመው።
ጥራት የተገባውን አሏህ በማውሳት የፍርሃት ፣ የድንጋጤ ፣ የጭንቀትና የሃዘን ደመናዎች ይበተናሉ፤ የትካዜ የችግርና የቁጭት ተራሮችም ይናዳሉ።
አሏህን አዘውትረው የሚያወሱ ሰዎች የህሊና እረፍትን ቢያገኙም አያስገርምም። ባይሆን እጅግ የሚገርመው እሱን ከማውሳት የተዘናጉ ሰዎች በህይወት መኖር መቻላቸው ነው።
አል-ቁርአን
ሱረቱ ነህል 16:21
«ህያው ያልሆኑ ሙታን ናቸው። መች እንደሚቀሰቅሱም አያውቁም።»
ህመም ተሰምቶህ ስሞታ የምታቀርበው ሆይ….. ስቃይ ደርሶብህ የምታለቅሰው ሆይ…. አደጋ አጋጥሞህ የደነገጥከው ሆይ…. አስከፊ ችግሮችም ያካበቡህ ሆይ…. በል በተቀደሰው ስሙ ተጣራ አምሳያም የለውም።
እሱን ባወሳህ ቁጥር ህሊናህ ያርፋል ፣ ልቦናህ ይረጋጋል ፣ ነፍስህም ትደሰታለች።
ምክኒያቱም እሱን ማውሳት ፣ በሱ መመካት ፣ በሱ መተማመንን ፣ በሱ ላይ ተስፋ መጣልን ፣ ወደ እሱ መመለስን ፣ ከሱ መልካምሙን ሁሉ መሻትን ፣ መፍትሄን ከሱ መጠበቅንም ያስገኛል።
እሱ ቢለመን ቅርብ ነው፤ ቢጠራ ሰሚ ነው፤ ቢጠየቅም ሰጭ ነው።
ስለዚህ ተናንሰህ ፣ ተዋርደህ ተዋደቅለት፤ የተባረከውንና የፀዳውን ስሙን በምላስህ እየደጋገምክ አወድሰው፤ አልቀው፤ ለምነው፤ ማርታንም ጠይቀው ደስታን ፣ ሰላምን ብርሃንን እና እርካታን ታገኛለህና።
አል-ቁርአን
ሱረቱል ኢምራን 3:148
«አሏህም የቅርቢቱን ምንዳና የመጨረሻይቱን መልካም ምንዳ ሰጣቸው።»
Share