የህይወት ጭንቀት፡ ኢስላማዊው መፍትሔ

Author picture
የዱንያ ልፋት ለምን አስጨነቀህ? እውነተኛው እረፍት ያለው የት እንደሆነ በማወቅ የህይወትህን አቅጣጫ አስተካክል።

መግቢያ

ሁላችንም በህይወት ሩጫ ውስጥ እንገኛለን። የተሻለ ኑሮ ፣ የተሻለ ገቢ ፣ ከችግሮች የጸዳ ህይወት እንመኛለን። ነገር ግን ይህ የማያቋርጥ ጥረት ብዙ ጊዜ ከድካምና ከጭንቀት ጋር የተቆራኘ ነው። እስኪ ቆም ብለን እንጠይቅ፤ የህይወት ጭንቀት በኢስላም ያለው እይታ ምንድን ነው? እውነተኛና ዘላለማዊ እረፍትስ የት ይገኛል?

ይህ ጽሑፍ የዚህችን ዓለም (ዱንያ) ተፈጥሮ ከፈጣሪያችን እይታ አንጻር በመዳሰስ ፣ የህይወት ጭንቀት አስወግደን እውነተኛ መረጋጋት የምናገኝበትን ነብያዊ መንገድ ይጠቁማል።

የዱንያን ፈተናዎች በጽናት አልፈን ለዘላለማዊው ቤታችን (አኺራ) እንዴት መዘጋጀት እንደምንችል እንማራለን።

የዱንያ ህይወት፡ የልፋትና የፈተና አገር

ሃያሉ አላህ በቅዱስ ቁርአኑ ላይ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-

“በእርግጥ ሰውን በልፋት ውስጥ ሆኖ ፈጠርነው።”

(ሱረቱል በለድ ፡90)

ይህ የቁርአን አንቀጽ የዚህችን ምድራዊ ህይወት ዋና መገለጫ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። ህይወት በማያቋርጥ ጥረትና ድካም የተሞላች ናት።

ብዙ ጊዜ ፍጹም እረፍትና መረጋጋትን በዚህች ዓለም ውስጥ ለማግኘት እንደልብ እንሮጣለን። ከጭንቀት ምንጮች ሁሉ ለመላቀቅ እንፈልጋለን።

ነገር ግን ልናስታውሰው የሚገባን ቁልፍ እውነታ ቢኖር ፍጹም እና ዘላለማዊ እረፍት በዚህች ምድር ላይ ሊገኝ እንደማይችል ነው።

አማኝ የሆነ ሰው ይህንን ስለሚረዳ ፣ አላህ ለደጋግ ባሮቹ ያዘጋጀላትን “ድካምና ልፋት የሌለባትን” የመኖሪያ ሐገር (ዳሩል መቃማ) ሁልጊዜ ያስታውሳል።

የአማኝና የማያምን ሰው የህይወት እይታ

የህይወትን ትርጉም መረዳት የምንኖርበትን ዓላማ ይወስነዋል።

አማኝ ያልሆነ ሰው፡ ህይወቱን በሙሉ ለምድራዊ ጥቅም ሲል ብቻ ሲለፋ ይኖራል። ለስሜቱ ባሪያ ይሆናል፤ ስሜቱን ካረካ በኋላም ለጭንቀትና ለልብ እረፍት እጦት ይዳረጋል።

በእውነቱ ይህ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ የላቀ ግብ ላይ ሳይደርስ በሩጫ በተሞላ ህይወት እንደኳተነ ይኖራል።

አማኝ የሆነ ሰው፡ የዚህችን ዓለም ፈተናዎች እንደ ጊዜያዊ መፈተኛ ይቆጥራቸዋል። እውነተኛ ግቡና መድረሻው መጪው ዓለም (አኺራ) መሆኑን ይረዳል።

የህይወት ጭንቀት እና ውጣ ውረዶች ሲያጋጥሙት በትዕግስት ያልፋቸዋል፤ ምክንያቱም ከዚህ ድካም ጀርባ ታላቅ ምንዳ እንዳለ ያውቃል።

የጭንቀት ምንጭ መቀየር፡ ከዱንያ ወደ አኼራ

ይህች ህይወት ባልተጠበቁ ክስተቶች የተሞላች ናት፤ አንድ ቀን በደስታ ስንፍለቀለቅ ፣ በቀጣዩ ቀን በሚያበሳጩ ነገሮች ልንከበብ እንችላለን። ይህን ተለዋዋጭ ባህሪ መገንዘብ ለመረጋጋት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ጭንቀትህን ለመጪው አለም (አኺራ) ካደረግክ ግን የሁለቱንም አለም መልካም ነገር ታገኛለህ፡፡ነገር ግን አብዛኛውን ጭንቀትህን ለዚህች አለም (ዱንያ) ካደረግክ ሁለቱንም ታጣለህ።

  • ዋና ጭንቀትህ ለአኺራ ሲሆን፡ የሁለቱንም ዓለም መልካም ነገር ታገኛለህ። አላህ ልብህን በሀብት (እርካታ) ይሞላዋል፣ የተበታተነ ጉዳይህን ይሰበስብልሃል፣ ዱንያም በራሷ ጊዜ ተዋርዳ ትመጣልሃለች።
  • ዋና ጭንቀትህ ለዱንያ ሲሆን፡ የሁለቱንም ዓለም ታጣለህ። ድህነት ከዓይኖችህ ስር አይለይም ፣ ጉዳዮችህ ይበታተናሉ ፣ ከዱንያም ቢሆን የተወሰነልህ እንጅ አታገኝም።

ከዚህ ህይወት እውነታዎች ሁሉ የላቀውና የማያጠራጥረው ሞት ነው። ስለዚህ በሚያበሳጩ ነገሮችና በልፋት በተሞላው ህይወትህ ከማልቀስ ይልቅ ስለ መጪው አለም (ስለ አኺራ) አስብ።

ዘላለማዊ ለሆነው የመጪው ዓለም ህይወት ማሰብ የብልህ ሰው ምርጫ ነው። አኺራ ሐዘንና ብስጭት የሌለባት፣ ፍጹም የመረጋጋትና የደስታ ዓለም ናት።

በተፈጥሯችን ይህችን ህይወት እንወዳታለን፤ ነገርግን ሃያሉ አላህ ይህችን ህይወት ዘላለማዊ መኖሪያ አላደረገልንም።

ሃያሉ አሏህ ከሚያበሳጩ ነገሮች የፀዳ ዘላለማዊ ህይወት ዘላለማዊ መኖሪያ (ዳረል መቃማ) ውስጥ ለደጋግ ባሮቹ አዘጋጅቷል። ሁኔታው እንዲህ ባይሆን ኖሮ  ሰዎች በዚህች ምድር ላይ እጅግ ባለፀጋ በሆኑ ነበር።

ነብያዊ መመሪያ፡ እውነተኛ ሀብትና መረጋጋት የቱ ነው?

ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ህይወት ትምህርቶችን እንውሰድ፡፡ ከቀደምት ትውልዶች ፣ ከምርጥ ሶሃቦች እና የእነሱን መመሪያና ፈለግ ከተከተሉት ህይወት ትምህርት እንውሰድ። ያጋጠሟቸው ችግሮች በመጪው ዓለም (አኺራ) ያላቸውን ከፍተኛ ደረጃ የሚያመለክቱ ናቸው።

ከነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) አንደበት የወጡት የሚከተሉት ሁለት ሐዲሶች የህይወትን አቅጣጫ ጠቋሚ ብርሃኖች ናቸው፡-

ከአነስ ኢብን ማሊክ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፦

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ትርሚዚ 2465)

“መጪው አለም (አኺራ) ዋና ጭንቀቱ የሆነ ሰው፤ አሏህ ሀብቱን በልቡ ውስጥ ያደርግለታል ፣ የተበታተነውን ጉዳዩን ይሰበስብለታል ፣ ምድራዊቱም ዓለም (ዱንያ) ተዋርዳ ትመጣለታለች። ምድራዊቱ አለም (ዱንያ) ዋና ጭንቀቱ የሆነ ሰው ደግሞ አሏህ ድህነቱን በዓይኖቹ መካከል ያደርግበታል ፣ የተሰበሰበውን ጉዳዩን ይበትንበታል ፣ ከዱንያም ለእሱ የተወሰነለት እንጅ አይመጣለትም።”

አብደላህ ኢብን መስኡድ (ረ.ዐ) የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ ሲሉ ዘግበዋል፦

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

(ኢብን ማጃ 4106)

“ጭንቀቶቹን ሁሉ አንድ ጭንቀት ያደረገ ሰው፤ ጭንቀቱም የመጪው ዓለም (አኺራ) የሆነ ሰው፤ ለምድራዊ ህይወቱ ጭንቀት አሏህ ይበቃዋል። ጭንቀቶቹ በዱንያ ጉዳዮች ላይ የተበታተኑበት ሰው ግን አሏህ በየትኛዋም የዱንያ ሸለቆ ውስጥ ቢጠፋ ግድ አይሰጠውም።”

ማጠቃለያ

የዱንያ ህይወት በልፋት የተሞላች መሆኗን መረዳትና መቀበል ለመረጋጋት ወሳኝ ነው። እውነተኛና ዘላለማዊ እረፍት የሚገኘው ዋና ትኩረታችንንና ጭንቀታችንን ወደ መጪው ዓለም (አኺራ) በማድረግ ነው።

የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መመሪያ እንደሚያሳየን ፣ ለአኼራችን ስንጨነቅ አላህ የዚህችን ዓለም ጉዳይ ቀላል ያደርግልናል።

የህይወት ጭንቀት እና ውጣ ውረዶች ሲያጋጥሙን ይህንን መለኮታዊ እውነት በማስታወስ እፎይታን እናግኝ።

በዚህ ርዕስ ላይ የእርስዎ አስተያየት እና ተሞክሮ ምንድን ነው? ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ያጋሩን።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share