የላ ኢላሀ ኢለሏህ ትርጉም እና የተውሒድ ምስጢር

Author picture
ላ ኢላሀ ኢለሏህ የሕይወት ቁልፍ ነው። የፍጥረትን ምስጢር፣ የእውነተኛ አምልኮን ምንነትና የዘላለምን ደስታ የያዘ የተውሒድ ቃል ነው።

መግቢያ

በእያንዳንዱ ሙስሊም ህይወት ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ የሚይዘው “ላ ኢላሀ ኢለሏህ” የሚለው ቃል እውነተኛ ትርጉሙ ምንድን ነው? ይህ ቃል ወደ ኢስላም መግቢያ በር ብቻ ሳይሆን አንድ አማኝ ከአምላኩ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚቀርጽ እና ህይወቱን በሙሉ የሚመራ የመንፈሳዊ ጉዞ መሠረት ነው። ብዙዎች በምላሳቸው ቢደጋግሙትም ፣ የላ ኢላሀ ኢለሏህ ትርጉም ከዚህ እጅግ የጠለቀ ነው።

ይህ ቃል የአላህን ጌትነት፣ አምላክነትና የባህሪያቱን ፍጹምነት መቀበል ነው።

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ፣ የዚህን የተውሒድ ቃል ጥልቅ ትርጉም፣ በአምልኮ ላይ ያለውን አንድምታ፣ እንዲሁም መላው ፍጥረት ለዚህ እውነት እንዴት እንደሚመሰክር ከቁርኣናዊ ማስረጃዎች ጋር እንመረምራለን።

የተውሒድ ቃል፡ የ “ላ ኢላሀ ኢለሏህ” መሰረታዊ ትርጉም

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ጋፊር 65)

‹‹እርሱ ህያው ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ሃይማኖትንም ለርሱ ብቻ አጥሪዎች ሆናችሁ ጥሩት፡፡››

አንድ ሰው ወደ እስልምና ማኅበረሰብ የሚገባበት ፣ ወደ ከፍተኛው የተውሒድ ደረጃ የሚደርስበት እና በአምልኮ መሰላል ላይ ከፍ የሚልበት የተውሒድ ቃል (ላ ኢላሀ ኢለሏህ) የሚለው ነው።

በዚህ ቃል ባሪያው የአላህን ጌትነት ፣ አምላክነት ፣ የስሞቹን እና የባህሪያቱን ፍፁምነት ይመሰክራል።

አምልኮ ለአሏህ ብቻ የተገባው መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ከእሱ ሌላ ማንም እንደሌለም ይመሰክራል።

ይህ የሆነበት ምክንያት በአፅናፈ አለሙ ውስጥ ያለው ሁሉ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ሰማያት ፣ ምድር ፣ ባህሮች ፣ ተራራዎች ፣ ዛፎች ፣ ወንዞች ፣ ሌሊትና ቀን ሁሉም ይመሰክራሉ።

ላ ኢላሀ ኢለሏህ ማለት ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ማለት ነው። አምልኮ ለእሱ ብቻ የተገባው ነው፡፡

ፍራቻ ፣ እርድ ፣ ተስፋ ፣ ሶላት ፣ ተስቢህ እና ሌሎችም ሁሉም የአምልኮ ዓይነቶች ለእሱ ብቻ የተገቡ ናቸው።

የፍጥረት ምስክርነት እና የአላህ አንድነት

ይህ የሆነበት ምክንያት እሱ ብቻውን ፍጥረታትን ካልነበረ ነገር በመፍጠርና በማስገኘት ፣ እንዲሁም በዓለም ላይ ያለውን ሁሉ በመፍጠር ፣ ህይወት በመስጠትና በመግደል ፣ ሲሳይን በመስጠትና በሌሎችም የጌትነቱ መገለጫዎች በመለየቱና ማንም በፍጥረታቱ አፈጣጠርም ሆነ በአንዳቸውም አስተዳደር ላይ ስላልተጋራው ነው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ኢብራሂም 32-34)

‹‹አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ፣ ከሰማይም ውሃን ያወረደ ፣ በእሱም ከፍሬዎች ሲሳይን ለእናንተ ያወጣ ፣ መርከቦችንም በፈቃዱ በባህር ላይ እንዲንቀሳቀሱ ለእናንተ የገራ ፣ ወንዞችንም ለእናንተ የገራ ነው። ፀሐይና ጨረቃ ያለማቋረጥ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ ለእናንተ ገራ፤ ሌሊትንና ቀንንም ለእናንተ ገራ። ከጠየቃችሁትም ሁሉ ሰጣችሁ፡፡ የአላህን ፀጋ ብትቆጥሩ አትዘልቁትም፡፡ ሰው በእርግጥ በጣም በዳይና ከሃዲ ነው።››

ይህ ደግሞ ባሪያው እሱን ብቻ በአምልኮ እንዲለይ ግዴታ አድርጎበታል።

ምክንያቱም እሱ እውነት ነው፤ ከእሱ ሌላ ያለው ሁሉ ውሸት ነው።

እውነተኛ አምልኮ በኢስላም እንዴት ይገለጻል?

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ሐጅ 6)

‹‹ይህ አላህ እሱ እውነት ስለሆነና ከእሱ ሌላ የሚጠሩት ሁሉ እሱ ውሸት ስለሆነ ነው።››

ሁሉን ቻይ የሆነው አሏህ እንዲህ ብሏል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ሐጅ 62)

‹‹ይህ አሏህ እሱ እውነት ስለሆነና ከእሱ ሌላ የሚጠሩት ሁሉ እሱ ውሸት ስለሆነና አላህም እሱ የላቀው ታላቁ ስለሆነ ነው።››

እሱ በራሱ የተብቃቃ ፣ የፀጋና የስጦታው ባለቤት ነው። እሱ በምድርም ሆነ በሰማይ ምንም የማያቅተው ቻይ ነው። እሱ ምንም ነገር የማይሰወርበት አዋቂ ነው።

‹‹ላ ኢላሀ ኢለላህ›› አላህን በውዴታ ፣ በክብር ፣ በማላቅ ፣ በፍራቻ ፣ በተስፋና በተያያዥ ጉዳዮች እንደ መመካት ፣ መመለስ ፣ መጓጓትና መፍራት መለየት ነው። እንዲሁም አላህን በልብ ፣ በምላስና በአካል ሥራዎች መለየት ነው።

ከእሱ ሌላ አይወድም፤ ባሪያው ሌላን ነገር ቢወድም ለጌታው ባለው ውዴታ ተከታይ ሆኖ ነው።

  • አንድ ሰው በአሏህ ስም ካልሆነ መማል የለበትም።
  • ከአሏህ በቀር ለማንም ስእለት አይሳልም።
  • ከአሏህ ትእዛዝ በቀር አይታዘዝም።
  • በችግር ጊዜ ከእሱ በቀር እርዳታ አይጠየቅም።
  • ከአላህ በቀር ለማንም አይሰግድም።
  • ከአላህ ውጭና በስሙ ካልሆነ በቀር አያርድም።
  • አጋር የሌለውን አሏህን ብቻ ያመልካል።

የቃልኪዳኑ ዋጋ፡ ከእሳት መዳን

ለዚህም ነው አሏህ ‘ላ ኢላሀ ኢለሏህ’ ብሎ በእውነትና በተግባር የመሰከረን ሰው እሳትን በእሱ ላይ እርም ያደረገው።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ የአላህን ፊት ፈልጎ ‘ላ ኢላሀ ኢለሏህ’ ያለን ሰው እሳትን በእሱ ላይ እርም አድርጓል።

አሏህ ልቦች የሚያመልኩት ፣ ነፍሶች የሚናፍቁት እና በጉጉት የሚጠብቁት ነው።

ወደ እሱ ይናፍቃሉ ፣ ይወዱታል ፣ እሱን በማውሳትና በመቅረብ ይደሰታሉ።

ፍጥረታት ሁሉ በእያንዳንዱ ቅጽበት ፣ በእያንዳንዱ ሀሳብና እይታ ወደ እሱ ይፈልጋሉ፡፡ እሱ የላቀው ታላቁ ጌታ አሏህ ነው።

ማጠቃለያ

ሲጠቃለል “ላ ኢላሀ ኢለሏህ” የኢስላም መሰረትና የተውሒድ ዋና ምሰሶ ነው። ይህ ቃል የአላህን አንድነት ከማወጅ ባለፈ ፣ የአንድን አማኝ ህይወት በሙሉ በአምልኮ ፣ በፍቅርና በፍራቻ ለእርሱ ብቻ እንዲገዛ ያደርጋል።

ይህንን ቃል በልባችን አምነን ፣ በምላሳችን መስክረን ፣ በተግባር ስንኖረው የዘላለም ደስታና ከእሳት መዳንን እናገኛለን።

ይህንን እውነት መረዳት የህይወታችንን ትልቁን ዓላማ መገንዘብ ነው።

በዚህ ርዕስ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? እባክዎ ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ያጋሩን።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share