የሽርክ አመጣጥ፡ የሰይጣን የመጀመሪያው ስኬታማ ሴራ

Author picture
ሽርክ የጀመረው በመልካም ሃሳብ ነበር። ሰይጣን የኑህን ህዝቦች በደረጃ ወደ ጥፋት የመራበትን አስገራሚ ታሪክ እና ዘላለማዊ ትምህርቱን ይወቁ።

መግቢያ

በምድር ላይ የመጀመሪያው ታላቅ ወንጀል የሆነው ሽርክ፣ የጀመረው በጥላቻና በክፋት ሳይሆን በመልካም ሰዎች ላይ በነበረ ጥልቅ ፍቅርና ክብር መሆኑን ያውቃሉ? የሰው ልጅ ታሪክ የጀመረው በአባታችን አደም (ዐ.ሰ) ንጹሕ ተውሒድ ላይ ነበር። ለአስር ክፍለ ዘመናት ምድር ከአላህ ውጭ ሌላን አታመልክም ነበር። ታዲያ ይህ ንጹሕ እምነት እንዴት ተበከለ? ይህ ጽሑፍ የሽርክ አመጣጥ የተከሰተበትን አስገራሚ ታሪክ ይተርካል።

ሰይጣን በኑህ ህዝቦች መካከል የተጠቀመበትን ስልትና በደረጃ በደረጃ የወሰዳቸውን “የሰይጣን እርምጃዎች” ከቁርአንና ከታማኝ የሊቃውንት ትንታኔ ጋር በማስረጃ አስደግፎ ያቀርባል።

ከብርሃን ወደ ጨለማ፡ የተውሒድ ዘመን ማብቃት

የሰው ልጅ በሙሉ በአንድ ሃይማኖት ላይ ነበር፤ እርሱም ኢስላም ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

አል-ቁርአን

(አል-በቀራህ፡ 213)

‹‹ሰዎች ሁሉ አንድ ሕዝብ ነበሩ››

በእርግጥም ሰዎች ከአባታችን አደም (ዐ.ሰ) ዘመን ጀምሮ ለአሥር ክፍለ ዘመናት ያህል በተውሒድ (በአሏህ አንድነት) ላይ ነበሩ። ከአሏህ በስተቀር ማንንም አያመልኩም ነበር፡፡ በምድር ላይም ምንም አይነት ሽርክ (ማጋራት) አልነበረም።

የኑህ (ዐ.ሰ) ህዝቦች ዘመን ሲመጣ በመካከላቸውም ለበጎ ነገር ቀዳሚ የሆኑ ደጋግ ሰዎች ነበሩ። እነሱም ወድ ፣ ሱዋዕ ፣ የጉሥ ፣ የኡቅ እና ነስር ሲሆኑ አሏህን የሚያመልኩና ለሰዎችም ጠቃሚዎች ነበሩ።

እነዚህ ደጋግ ሰዎች ሲሞቱ ህዝቦቻቸው አዘኑ። የመልካም ነገር አርአያዎቻቸውን አጡ። ይህ ሀዘን ለሰይጣን ሴራ ምቹ በር ከፈተለት።

የሰይጣን እርምጃዎች፡ ሴራው በደረጃ ሲተገበር

የሽርክ አመጣጥ በተመለከተ ሰይጣን የኑህን ህዝቦች በአንድ ጊዜ “ጣዖት አምልኩ” አላላቸውም፤ ይህን ቢል ኖሮ ማንም አይቀበለውም ነበር።

ይልቁንም፣ አላህ ያስጠነቀቀንን “የሰይጣን እርምጃዎች” በመከተል ቀስ በቀስ ወደ ጥፋት መራቸው።

ደረጃ 1: የመልካም ሃሳብ ጉትጎታ

ሰይጣን ወደ አዘኑት ሰዎች በመምጣት እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ምስሎቻቸውን ብትቀርጹና ባያችኋቸው ቁጥር እነሱን እያስታወሳችሁ በአምልኳችሁ ላይ ትነቃቃላችሁ፤ በመታዘዝም ትጨምራላችሁ›› በማለት ጉትጎታ አደረገባቸው።

ሀሳቡ በመልካምነት የተሸፈነ ነበር፤ ዓላማው አምልኮን “ለማገዝ” ይመስል ነበር። እነሱም ሰይጣንን በመታዘዝ አምልኮንና መልካም ነገርን ለማስታወስ ምስሎቻቸውን ቀረጹ።

ደረጃ 2: የትውልድ መተካትና የእውቀት መረሳት

ዓመታት አለፉ፤ ምስሎቹን የቀረጸው ትውልድ አልፎ ሌላ ትውልድ ተተካ። የቀድሞዎቹ አባቶች ምስሎቹን ለምን እንዳቆሙ እውነተኛው እውቀት ቀስ በቀስ እየደበዘዘና እየተረሳ መጣ። ምስሎቹ ግን አሁንም በቦታቸው ነበሩ።

ደረጃ 3: የውሸት ትርጓሜና የአምልኮ ጅማሮ

እውቀት ከተረሳ በኋላ ሰይጣን ወደ አዲሱ ትውልድ በመምጣት እንዲህ አላቸው፡- “አባቶቻችሁና አያቶቻችሁ ዝናብ ሲፈልጉ በእነዚህ አማልክት ይለምኑ ነበር፤ እነርሱም ያዘንቡላቸው ነበር።

እነርሱ የሚያመልኳቸው ነበሩ።” በዚህ የውሸት ትርጓሜ፣ የመጀመሪያው ትውልድ ለመልካም ማስታወሻ ያቆመው ሀውልት፣ በሶስተኛው ትውልድ የአምልኮ ጣዖት ሆነ።

መለኮታዊ ምላሽ፡ የኑህ (ዐ.ሰ) ጥሪ

ሽርክ በምድር ላይ ሲስፋፋ ሃያሉ አሏህ ኑህን (ዐ.ሰ) ወደ ህዝቦቹ ላከው፡፡ አሏህን በብቸኝነት እንዲያመልኩና ሽርክን እንዲያስጠነቅቃቸው አዘዘው። ጥሪውም አንድና ግልጽ ነበር፤ ወደ ተውሒድ መመለስ።

ሁሉን ቻይ የሆነው አሏህ እንዲህ ይላል፡-

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አዕራፍ፡ 59)

‹‹ኑህን ወደ ሕዝቦቹ በእርግጥ ላክነው። አላቸውም፡- ‹ሕዝቦቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ከእሱ ውጭ ሌላ ለእናንተ አምላክ የላችሁምና። በእናንተ ላይ አስጨናቂ የሆነችን ቀንን ቅጣት እፈራላችኋለሁና።››

አሏህ ኑህን (ዐ.ሰ) ሰዎችን ወደ ቀጥተኛው መንገድና ወደ ትክክለኛው አካሄድ እንዲመልስ የላከው ቢሆንም ሃያሉ አሏህ የነበረው ክስተት ሲነግረን እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ኑህ፡ 23)

‹‹አሉም፡ ‹አምላኮቻችሁን አትተዉ። ወድንም ፣ ሱዋዕንም ፣ የጉሥንም ፣ የኡቅንም፣ ነስርንም አትተዉ።››

ኢብኑ አባስ (ረ.ዐ) እንዲህ አሉ፡ ‹‹እነዚህ ከኑሕ ህዝቦች የነበሩ የደጋግ ሰዎች ስሞች ናቸው። በሞቱ ጊዜ ሰይጣን ለህዝቦቻቸው ‹በተቀማመጥባቸው የነበሩ ቦታዎች ላይ ሐውልቶችን አቁሙላቸውና በስማቸው ሰይሟቸው› በማለት አመለከተላቸው።

እነሱም አደረጉት፤ ነገር ግን አላመለኳቸውም። ያ ትውልድ ካለፈና እውቀት ከተረሳ በኋላ ግን መመለክ ጀመሩ።››

ሰይጣን ወደ እነሱ የመጣው በፍቅር ፣ መልካም ነገርን በመስራት ፣ በማስዋብና በጉትጎታ ሰበብ ነበር። ይህ ደግሞ በሁሉም የአደም ልጆች ላይ የሚከተለው መንገድ ነው።

ሰይጣን የኑህን ህዝቦች ከአሏህ ውጭ ሌላን እንዲያመልኩ በአንድ ጊዜ አልጠየቃቸውም። ይህን ቢያደርግ ኖሮ ማንም አይቀበለውም ነበር። ነገር ግን በዚህ አደገኛ ቁልቁለት ላይ ደረጃ በደረጃ ወሰዳቸው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ኑር፡ 21)

‹‹የሰይጣንን እርምጃዎች አትከተሉ።››

ከዚህ በመነሳት ሙስሊም የሆነ ሰው ወደ ሽርክና ክህደት ከሚመሩ የሰይጣን እርምጃዎች ፣ ተንኮሎች ፣ ስልቶችና ማታለያዎች መጠንቀቅ አለበት።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ፋጢር፡ 6)

‹‹ሰይጣን ለእናንተ ጠላት ነውና ጠላት አድርጋችሁ ያዙት። ተከታዮቹን የሚጠራ የሳት ጓዶቹ እንዲሆኑ ብቻ ነው፡፡››

ሃያሉ አሏህ እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ያሲን፡ 62)

‹‹ከእናንተም ብዙ ፍጥረታትን በእርግጥ አጥንቷል። ታዲያ አታውቁምን?››

ታዲያ ሰይጣን የኑሕን (ዐ.ሰ) ህዝቦች ለማጥመም የተጠቀመባቸው ስልቶች ምንድን ናቸው?

ማጠቃለያ

የሽርክ አመጣጥ ታሪክ ትልቁ ትምህርት ፣ ሰይጣን ወደ ጥፋት የሚጠራው በቀጥታ ሳይሆን በመልካም በሚመስሉ “እርምጃዎች” መሆኑን ነው።

በደጋግ ሰዎች ላይ የነበረው ፍቅር ወደ ማጋነን ሲቀየር፣ ያ ማጋነን ደግሞ ወደ አምልኮ ሲሸጋገር የሰው ልጅ የመጀመሪያውን ታላቅ በደል ፈጸመ።

ስለዚህ እያንዳንዱ ሙስሊም ወደ ሽርክ ሊከፍቱ የሚችሉ ትንንሽ የሚመስሉ በሮችን ሁሉ በጥብቅ መጠንቀቅና መዝጋት አለበት።

ከዚህ ታሪክ በመነሳት በዘመናችን ልንጠነቀቃቸው ይገባል ብለው የሚያስቧቸው “የሰይጣን እርምጃዎች” የትኞቹ ናቸው? በውይይቱ ይሳተፉ።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share