ተውሒድ፡ የአንድ ባሪያና የተበታተኑ ጌቶች አስደማሚ ምሳሌ

Author picture
የአንድ ጌታ ባሪያ ወይስ የብዙ ጌቶች ባሪያ? ቁርኣን በተውሒድ እና በሽርክ ላይ ያስቀመጠውን ይህን አስደማሚ ምሳሌ በማንበብ የእምነትዎን ሰላም ይረዱ።

መግቢያ

አንድ ሰራተኛ በብዙ፣ እርስበርስ በሚሻኮቱና በሚጋጩ አለቆች ስር ቢሰራ ህይወቱ ምን ይመስላል? የትኛውን ትዕዛዝ ያስቀድም? የማንን ውዴታስ ለማግኘት ይጣጣር? ይህ ምስል በውጥረትና በውዥንብር የተሞላ ነው። ሃያሉ አሏህ በቅዱስ ቁርአኑ ፣ ከአርሹ በላይ ሆኖ፣ የሽርክን (በእርሱ ላይ ማጋራትን) ሁኔታ ከዚህ ጋር ያመሳስለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ተውሒድ (አላህን በብቸኝነት ማምለክ) የሚያጎናጽፈውን የአእምሮ ሰላምና የመንፈስ እርጋታ በአንድ ጌታ ስር በሚሰራ ታማኝ ባሪያ ይመስለዋል።

ይህ ጽሑፍ አላህ (ሱ.ወ) በቁርአኑ ውስጥ የተጠቀመባቸውን ሁለት ልብ የሚነኩ ምሳሌዎች በመፈተሽ፣ የተውሒድን ክብርና የሽርክን ውድቀት ያሳየናል።

የደረቀ ተስፋ፡ ውሃ እንደማይደርሰው የተጠማ ሰው ምሳሌ

አሏህ ሁል ጊዜ ባሮቹ ተውሒድን (አላህን በብቸኝነት ማምለክን) ለእሱ ብቻ እንዲያደርጉና ከእሱ ውጭ ያለን ነገር ሳይሆን እሱን ብቻ እንዲያመልኩ ያዛል፡፡

ሁልጊዜም ከሽርክ (ማጋራት) ይከለክላል፤ አስቀያሚነቱን እና ውድቅነቱንም ግልጽ በሆኑ ምሳሌዎችና በእውነተኛ ማስረጃዎች ይገልፃል፡፡ ከእነዚህ ምሳሌዎች መካከል ይህ የሃያሉ አሏህ ነው፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ረዕድ 14)

‹‹የእውነት ፀሎት ለእሱ ብቻ ነው፡፡ እነዚያ ከእሱ ሌላ የሚጠሯቸው (ጣዖታት) ምንም አይመልሱላቸውም፡፡ የሚጠራቸው ሰው ምሳሌ ውሃ ወደ አፉ ይደርስ ዘንድ ሁለት እጆቹን ወደ እሱ እንደዘረጋ ሰው ነው፤ ነገር ግን ፈጽሞ አይደርስለትም፡፡ የከሃዲዎችም ፀሎት በከንቱ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡››

ሃያሉ አሏህ በዚህ ምሳሌ ከእሱ ውጭ የሚመለኩ የሐሰት አማልክት ምን ያህል አቅመ ቢስና ደካማ እንደሆኑ ያብራራል፡፡

እንዲሁም አጋሪው ከእነሱ ፈጽሞ መጠቀም እንደማይቻል እና ፀሎቱም ሆነ አምልኮው ምንም እንደማይፈይድለት ይገልፃል፡፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ማኢዳ፡ 76)

‹‹በላቸው! ከአላህ ሌላ የማይጎዳችሁንና የማይጠቅማችሁን ትግገዛላችሁን? አላህ ሁሉን ሰሚ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡››

ይህ ምሳሌ እጅግ አስደናቂ ነው።

የአጋሪው ሁኔታ፡ ከአላህ ውጭ ያሉ አማልክትን የሚለምን ሰው፣ በከፍተኛ ጥም ተይዞ ውሃን ከሩቅ እያየ እጆቹን በዘረጋ ሰው ይመሰላል። ጥሙ እውነተኛ ነው፣ ፍላጎቱም ከባድ ነው።

የውሸት አማልክቱ ምላሽ፡ ልክ ውሃው ለተጠማው ሰው እጅ መድረስ እንደማይችለው ሁሉ ፣ የውሸት አማልክትም ለተማጸኗቸው ሰዎች ምንም ሊፈይዱ አይችሉም።

ጉዳትን ማስወገድም ሆነ ጥቅም ማስገኘት አይችሉም። ጸሎቱም ፣ ልመናውም ፣ አምልኮውም ሁሉ ከንቱ ድካም ነው።

በተመሳሳይ መልኩ አጋሪውም በቋሚ ጥምና ችግር ፣ በመከራና በጭንቀት ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የፈጠረውን እና ያስገኘውን እውነተኛ አምላክ ትቶ የሐሰት አማልክትን ስላመለከ ነው፡፡

ይህን ዓለም ብቻውን የፈጠረውን ፣ ጉዳትና ጥቅም በእጁ የሆነውን አምላክ ትቷል፡፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ዩኑስ፡ 31)

‹‹ከሰማይና ከምድር ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማን ነው? መስሚያዎችንና ማያዎችንስ የፈጠረ ማን ነው? ከሙትም ህያውን የሚያወጣ ፣ ከህያውም ሙትን የሚያወጣ ፣ ነገሩንም ሁሉ የሚያስተናብር ማን ነው? በላቸው፡፡ «አላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «ታዲያ አትጠነቀቁም?» በላቸው፡፡››

ሰላምና ውዥንብር፡ የአንድ ባሪያና የብዙ ጌቶች ምሳሌ

  • የአጋሪው (የሙሽሪኩ) ምሳሌ

አሏህ ከእሱ ውጭ አማልክትን የሚያመልከውን አጋሪ ሰው ብዙ የተለያዩ አለቆች ካሉት ተቀጣሪ ወይም ሠራተኛ ጋር ያመሳስለዋል፡፡

እያንዳንዱ አለቃ በተመሳሳይ ሰዓት ከሠራተኛው የሚፈልገው የተለየ ጥያቄ አለው፡፡ ይህ ሠራተኛ እርስ በርሳቸው በሚጣሉና በሚለያዩ አለቆቹ መካከል ሲዋልል ሁኔታው እንዴት ይሆናል?

ይህኛው አለቃ ሌላኛውን የሚፃረር ትእዛዝ ይፈልጋል፤ ያኛው ደግሞ ከባልደረባው ፍላጎት በተቃራኒ የሆነ ነገር ይፈልጋል፤ ሠራተኛውም ግራ በመጋባት ውስጥ ሆኖ የትኛውን ትእዛዝ መፈጸም እንዳለበት ግራ ይገባዋል፡፡

ጥያቄዎቻቸውን በአንድ ጊዜ ማሟላት ፈጽሞ የማይቻል ነው፡፡ የተለያዩ አማልክትን የሚያመልክ ሰው ሁኔታ እንዲሁ ነው፡፡

በጭንቀት ፣ በሐዘንና በመከራ ውስጥ ነው፤ ፈጽሞ የእነሱን ውዴታ ሊያገኝ አይችልም፡፡

  • የአንድ አምላክ አምላኪ (የሙወሒዱ) ምሳሌ

አሏህን ብቻ የሚያመልክና ተውሒድን የሚያራምድ ሰው ምሳሌው አንድ አለቃ ብቻ እንዳለው ሠራተኛ ነው፡፡

ከተለያዩ አለቆችና ባልደረቦች ግጭት የፀዳ እረፍት አለው፡፡ የአለቃውን ውዴታ የሚያገኝበትን መንገድ ያውቃል፤ ጥያቄዎቹን ያሟላል፤ ግዴታውንም በተሻለ ሁኔታ ይወጣል፤ ከአለቃውም ርህራሄና አዘኔታን ያገኛል፡፡

ታዲያ እነዚህ ሁለት ሠራተኞች እኩል ይሆናሉ? ሃያሉ አሏህ እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ዙመር፡ 29)

‹‹አሏህ ምሳሌን አደረገ፡- አንድ ሰው በእሱ ላይ የሚጨቃጨቁ ተጋሪዎች ያሉት ሲሆን ሌላውም ሰው ለአንድ ሰው ብቻ ንፁህ የሆነ ባሪያ ቢሆን፤ በምሳሌነታቸው እኩል ይሆናሉን? ምስጋና ለአሏህ የተገባ ነው፡፡ አብዛኞቻቸው ግን አያውቁም፡፡››

ማጠቃለያ

በእነዚህ የቁርአን ምሳሌዎች እንደተመለከትነው፣ ተውሒድ (አላህን በብቸኝነት ማምለክ) የህይወት መመሪያን በማቅናት ለአእምሮ ሰላምና ለመንፈስ እርጋታ ብቸኛው መንገድ ነው።

ሽርክ ደግሞ ህይወትን በውዥንብር ፣ በተበታተነ ዓላማና በማያቋርጥ ጭንቀት የሚሞላ የጥመት መንገድ ነው።

ምርጫው ግልጽ ነው፤ በአንድ አዛኝ ጌታ ስር ሆኖ መረጋጋት ወይስ እርስበርስ በሚጋጩ የውሸት አማልክት መካከል ሆኖ መዋልል? አላህ ሁላችንንም በተውሒድ ላይ ያጽናን።

ከእነዚህ የቁርአን ምሳሌዎች እርስዎ የተማሩት ትልቁ ትምህርት ምንድን ነው? ሀሳብዎን ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ላይ ያካፍሉን።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share