ሽርክ በኢስላም፡ ይቅር የማይባለው ታላቁ በደል

Author picture
ከወንጀሎች ሁሉ የከፋው፣ መልካም ስራን ሁሉ ውድቅ የሚያደርገውና የአላህን ምህረት የሚዘጋው ታላቁ በደል ሽርክ ነው። ከዚህ አስከፊ ወንጀል እራስዎን ይጠብቁ።

መግቢያ

በኢስላም አስተምህሮ ፍትህና በደል ግልጽ የሆነ መለኪያ አላቸው። ፍትህ ሁሉንም ነገር በተገቢው ስፍራ ማስቀመጥ ሲሆን ከፍትሆች ሁሉ የላቀው ደግሞ አምልኮን ለብቸኛው ፈጣሪ ለአላህ ብቻ ማድረግ (ተውሒድ) ነው። በሌላ በኩል ሽርክ በኢስላም ከበደሎች ሁሉ የከፋው “ታላቁ በደል” ተብሎ ይጠራል።

ይህ ጽንሰ-ሀሳብ ጣዖትን ከማምለክ የሰፋ ትርጉም አለው፤ እሱም የፈጣሪን መብት ለፍጡር አሳልፎ መስጠት ነው።

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሽርክን ምንነት ፣ ስራን እንዴት እንደሚያበላሽ ፣ ለምን ይቅር የማይባል ወንጀል እንደተባለና አማኙ ሊኖረው የሚገባውን ጥንቃቄ ከቁርአናዊ ማስረጃዎች ጋር እንመለከታለን።

“ታላቁ በደል”፡ የሽርክ ትርጉም እና ምንነት

በደል የብልሹነት ፣ የውድመትና የጥፋት መንስኤ ነው። በደል ማለት በመብቶች ላይ ወሰን ማለፍና ከእውነት መውጣት ነው።

የአሏህ መብት እሱን በብቸኝነት ማምለክ (ተውሒድ) ነው፡፡ ተውሒድ ፍጹም ፍትህ ሲሆን ሽርክ (ማጋራት) ደግሞ ከሁሉ የከፋ በደልና አስቀያሚ ድንቁርና ነው።

ምክንያቱም የዓለማትን ጌታ ማሳነስ ፣ እሱን ከመታዘዝ መኩራትና ለእሱ ብቻ የሚገባውን መብት ለሌላ አሳልፎ መስጠት ነውና።

ከአሏህ ውጭ ሌላን ያመለከ ሰው አምልኮቱን ተገቢ ባልሆነ ስፍራ ላይ አስቀምጧል።

አል-ቁርአን

(ቁርአን 31፡13)

‹‹ሉቅማን ልጁን ሲገስፅ እንዲህ አለ፡ ’ልጄ ሆይ! በአሏህ ላይ አታጋራ፤ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና’ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡»

በሃያሉ አሏህ ቃል ውስጥ «በአላህም ላይ አንድንም አትጥሩ»)  ‘አንድንም’ የሚለው ቃል ክልከላን በሚያመለክት አውድ ውስጥ ያልተወሰነ (ነኪራ) ሆኖ በመምጣቱ ከአላህ ውጭ ያለን ማንኛውንም አካል ያጠቃልላል።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ጅን ፡18)

«መስጅዶች የአሏህ ብቻ ናቸው፡፡ በአላህ ላይ አንድንም አትጥሩ፡፡»

መላዕክትን ፣ ነብያትን ፣ ጅኖችን ፣ ሰዎችን ፣ ጣዖታትን ፣ ዛፎችን ፣ እንስሳትን ፣ ድንጋዮችን ፣ ቀብሮችን ፣ ሙታንንና ፍጥረታትን በሙሉ ያካትታል።

ይቅር የማይባል ወንጀል፡ የሽርክ አስከፊ መዘዝ

የሽርክ አደጋ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ፣ አንድ ሰው በሽርክ ላይ ሆኖ ከሞተና በህይወት እያለ ንስሐ ካልገባ አላህ በፍጹም ይቅር የማይለው ብቸኛው ወንጀል ነው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ኒሳዕ፡ 48)

«አሏህ በእሱ ላይ ማጋራትን አይምርም፤ ከዚያ ውጭ ያለውንም (ሃጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡»

ከዚህም በላይ በአላህ ላይ ማጋራት መልካም ሥራዎችን ሁሉ የሚያበላሽና አምልኮን ውድቅ የሚያደርግ ነው።

አላህ ለታላቁ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንኳ እንዲህ የሚል ከባድ ማስጠንቀቂያ አውርዷል፡-

ከሱረቱ ዙመር የሆኑትን እነዚህን የተከበሩ አንቀፆች ልብ ብለህ አድምጥ፤ ይህ ተቃውሞ በዚህ አውዱ ወስጥ እንዴት እንዳመጣ አስተንትን።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ዙመር፤ 64)

«እናንተ መሃይማን ሆይ! ከአላህ ሌላን እንዳመልክ ታዙኛላችሁን?’ በላቸው፡፡»

ይህ ታላቅ በደልን የሚያወግዝ ጥያቄ ነው።

ይህ ማለት የአሏህን አንድነትና ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ እሱ ብቻውን መፍጠሩን የሚያመለክቱ ምልክቶችን ካያችሁ በኋላ እንዲሁም ከእሱ የማደርሰውን እውነተኝነቴን ከተመለከታችሁ በኋላ፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ከአላህ ሌላን እንዳመልክ ታዙኛላችሁን? እናንተ የአላህን መብት የማታውቁ መሃይማን ሆይ! የአላህን ታላቅነት የማታውቁ መሃይማን ሆይ! እናንተ የእሱን ልክና ሃይል የማታውቁ መሃይማን ሆይ!

  • አንድ ሰው ከአሏህ ውጭ ሌላ ፈጣሪ ወይም ረዳት እንዳለ ባመነ ጊዜ በእርግጥም አጋርቷል።
  • አንድ ሰው ከአላህ ውጭ ሌላ አካል አምልኮ ይገባዋል ብሎ ባመነ ጊዜ እሱ ሙሽሪክ (አጋሪ) ነው።
  • አንድ ሰው አሏህ በስሞቹና በባሕርያቱ አምሳያና አቻ አለው ብሎ ባመነ ጊዜ እሱ ሙሽሪክ (አጋሪ) ነው።

ከዚያም ማስጠንቀቂያው ለፍጥረታት ምርጦችና ለቅኑ መንገድ መሪዎች (በእነሱ ላይ የአላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ) ይመጣል። በእርግጥም ወደ አንተም ወደ እነዚያም ከአንተ በፊት ወደነበሩት እንዲህ ሲል ተወርዷል፡-

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ዙመር፤ 65)

«ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፤ በእርግጥም ከከሳሪዎቹ ትሆናለህ፡፡»

የተዘጋው የምህረት በር፡ በሽርክ እና በሌሎች ወንጀሎች መካከል ያለው ልዩነት

ሽርክ ለባለቤቱ ምሕረት የሌለው በመሆኑ ከሌሎች ወንጀሎች የሚለይ ብቸኛ ወንጀል ነው። ሌሎች ወንጀሎች ግን ባለቤታቸው ንስሐ ሳይገባ ከሞተ በአሏህ ፈቃድ ሥር ነው፤ አሏህ ከፈለገ ይምረዋል፤ ከፈለገም ይቀጣዋል።

አሏህ ከሽርክ በታች ላሉ ወንጀሎች ብዙ የምሕረት ማግኛ መንገዶችን አስቀምጧል። ለምሳሌ

  • ወንጀልን የሚያብሱ መልካም ሥራዎች
  • ሃጢአትን የሚያሰርዩ መከራዎች
  •  የአማላጆች ምልጃና የሙስሊሞች ዱዓ

ይህ ሁሉ አላህ ለተውሒድ ሰዎች ካለው ልዩ እዝነት ነው። በሽርክ ላይ ላለ (ሙሽሪክ) ግን እነዚህ የምህረት በሮች ሁሉ ዝግ ናቸው።

ያለ ተውሒድ የሚሰራው መልካም ስራም ምንም አይጠቅመውም።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ማኢዳ ፡ 72)

‹‹በአሏህ ላይ የሚያጋራ ሰው አሏህ በሱ ላይ ጀነትን እርም አድርጓል፤ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ረዳቶች የሏቸውም፡፡››

ማጠቃለያ

ሲጠቃለል ሽርክ በኢስላም የአላህን ብቸኛ መብት የሚጋፋ ታላቁ በደል ነው። መልካም ሥራን ሁሉ ከንቱ የሚያደርግና ያልተጸጸቱበት እንደሆነ የዘላለም ኪሳራን የሚያስከትል ብቸኛው ወንጀል ነው።

ስለዚህ እያንዳንዱ ሙስሊም የተውሒድን ምንነት አውቆ ከሁሉም የሽርክ አይነቶች እራሱን መጠበቅ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ግዴታው ነው።

የተውሒድን ህይወት ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትልቁ ፈተና ምንድን ነው? ሀሳብዎን በአስተያየት መስጫው ላይ ያጋሩን።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share