የዱዓ ሃይል ፡ በችግር ጊዜ የማይከዳው መፍትሔ

Author picture
የተዘጉ በሮችን የሚከፍትልህ፣ ከጭንቀት የሚያወጣህ አንድ ኃይል አለ። የዱዓን ሃይል ተጠቅመህ ከአላህ ጋር በቀጥታ ተገናኝ።
የዱዓ ሃይል

መግቢያ

በህይወታችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ፣ የዓለም ሃሳብና ጭንቀት ጫንቃችን ላይ ሲከመር ፣ መንገዶች ሁሉ የተዘጉ ሲመስሉን ወደ ማን ነው የምንዞረው? ብዙ ጊዜ በፍርሃትና በጭንቀት ተውጠን መፍትሔው ከእኛ ጋር መሆኑን እንዘነጋለን። የዱዓ ሃይል በኢስላም ያለው ትርጉም ይኸው ነው።

ዱዓ ከፈጣሪያችን ጋር የምንነጋገርበት ፣ ችግሮቻችንን የምናፈስበትና እርዳታውን የምንጠይቅበት ቀጥተኛ መስመር ነው። ይህ ጽሑፍ ዱዓ ተራ ልመና ሳይሆን ፣ ዱአ የአንድ አማኝ ትልቁ መሳሪያ እና የማይነጥፍ የተስፋ ምንጭ መሆኑን ያስታውሰናል።

የአላህን (ሱ.ወ) ቅርበትና የገባልንን ቃል ኪዳን በማስታወስ እውነተኛ መረጋጋትን እንዴት ማግኘት እንደምንችል እንመለከታለን።

የፈጣሪ ጥሪና የሰው ልጅ ምላሽ

ሃያሉ አላህ በቅዱስ ቁርአኑ ላይ ግልጽና የማያሻማ ጥሪ አስተላልፎልናል፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ጋፊር፡ 40)

ጌታችሁም አለ፡- «ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና፡፡ እነዚያ እኔን ከመገዛት የሚኩራሩ (የሚንጠባረሩ) በእርግጥ የተዋረዱ ሆነው ጀሐነም ይገባሉ»፡፡

ይህ መለኮታዊ ጥሪ ራሱ ታላቅ እዝነት ነው። ጥያቄው ግን እኛ ይህንን ጥሪ እንዴት እየተቀበልነው ነው?

በችግር ጊዜ፡ በህይወትህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ… የምትለምነው ማንን ነው? ያሰብካቸው እቅዶችህ ሁሉ ሲከሽፉና ተስፋ ስትቆርጥ የምትመካው በማን ላይ ነው?

በጭንቀት ሰዓት፡ የአለም ሃሳብና ጭንቀት ሁሉ በአንተ ጫንቃ ላይ የወደቀ ሲመስልህ… ለመረጋጋት የምትጠጋው ማንን ነው? መንገዶች ሁሉ የተዘጉብህ ሲመስልህ… የምትከጅለውና ተስፋ የምታደርገው በማን ላይ ነው?

በብዙ አጋጣሚዎች ፍርሃቶቻችንና ጭንቀቶቻችን እንዲቆጣጠሩን እድል እንሰጣለን፤ አሏህ (ሱ.ወ) እዚሁ ቅርብ መሆኑን ግን ብዙ ጊዜ እንዘነጋለን፡፡ ነገር ግን ጉዳያችን እንዲቃለል ፣ ልባችን እንዲረጋጋ ከፈለግን ብቸኛው መፍትሔ እሱን መለመን ፣ በእሱ ላይ መመካትና መተማመን ነው። ከፈጠረህ በላይ የአንተን ሁኔታ የሚያውቅና የሚረዳህ ማንም የለምና። ዋናው ነገር… ችግሮች ፣ ፍላጎቶች እና መከራዎች ሲያጋጥሙህ መጀመሪያ እሱን ታስታውሰዋለህ? ወይ የሚለው ነው፡፡

የመጀመሪያ ምርጫህ አላህ ነውን?

አንድ አማኝ ሊጠይቀው የሚገባው ቁልፍ ጥያቄ አለ፦ ችግሮች ፣ ፍላጎቶች እና መከራዎች ሲያጋጥሙህ በመጀመሪያ የምታስታውሰው ማንን ነው? ብዙ ጊዜ መፍትሔ ፍለጋ ወደ ሰዎች ፣ ወደ ገንዘባችን ወይም ወደ እውቀታችን እንሮጣለን። እነዚህ ሁሉ ግን ውስንና አላፊ ናቸው። ዘላለማዊና የማይከዳው ኃይል የአላህ ብቻ ነው።

  • ፍጥረታቱን ከጨለማ አውጥቶ ወደ ብርሃን የሚሻግረው ማን ነው?
  • የምትመኘውን ነገር ሁሉ ሊሰጥህ የሚችለውስ ማን ነው?
  • ከግዛቱ ምንም ሳያጎድል ሁኔታህን ሊለውጥና የልብህን መሻት ሊሰጥህ የሚችለው ማን ነው?

መልሱ አንድና አንድ ነው፤ አላህ! እሱ ለነገሩ «ሁን» ይለዋል፤ ወዲያውኑም ይሆናል።

የማይናወጠው ምሰሶ፡ የአላህ የተስፋ ቃል

ምሰሶዎች ሁሉ ቢከዱህ እና ሊያጠፉህ ቢታገሉ እጆችህን አንሳና በአሏህ ተጠበቅ፤ እሱ የማይናወጥ ምሰሶ ነውና፡፡ በሌሊትም በቀንም ፣ በችግርህም ሆነ በድሎትህ ለምነው፡፡ ከምትፈራው ነገር ሁሉ በእሱ ተጠበቅ፡፡ የእሱንም ቃል አስታውስ፡-

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ፡ 186)

«ባሮቼም ስለ እኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለመነኝን ሰው ልመናውን በለመነኝ ጊዜ እቀበላለሁ፡፡ ለእኔ ትእዛዝ ምላሽ ይስጡ፤ በእኔም ይመኑ፤ ምናልባት ወደ ቅኑ መንገድ ይመሩ ይሆናልና፡፡»

ማጠቃለያ

ዱዓ አማራጭ የሌለው አማኝ የመጨረሻው ተስፋው ሳይሆን ፣ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ የመጀመሪያውና ዋነኛው መፍትሔው ነው። የአላህ (ሱ.ወ) በር ሁሌም ክፍት ነው፤ እሱ ከእኛ የሚፈልገው ከልብ የመነጨ ልመናን እና በእርሱ ላይ ሙሉ እምነት መጣልን ብቻ ነው። ስለዚህ በህይወት ፈተናዎች ውስጥ ስታልፍ ተስፋ አትቁረጥ፤ ይልቁንም እጆችህን ወደ ላይ አንስተህ በሙሉ እምነት ለምን። እሱ ሰሚና ቅርብ ነውና።

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share