መግቢያ
የምንመርጣቸው ጓደኞች የህይወታችንን አቅጣጫ ከመወሰን አልፎ ማንነታችንን የመቅረጽ ሀይል አላቸው። እነሱ የዲናችንና የባህሪያችን ነጸብራቆች ናቸው። በዚህም ምክንያት፣ መልካም ጓደኝነት በኢስላም ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውና የእምነታችን አንድ አካል ተደርጎ የሚቆጠር ጉዳይ ነው።
በህይወት ጉዟችን ውስጥ አንዳንዶች እንደ ብርሃን ሆነው መንገዳችንን ሲያደምቁ፣ ሌሎች ደግሞ እንደ ጥቁር ደመና ሆነው የህይወት ብርሃናችንን ይጋርዳሉ። ይህ ጽሑፍ በኢስላም ሚዛን ጓደኝነትን ይመዝናል፤ ወደ አላህ የሚያቀርቡንን ወዳጆች እንድንመርጥና ከእርሱ ከሚያርቁን እንድንሸሽ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ድንቅ አስተምህሮት ያስቃኘናል።
የጓደኝነት ሁለት ገጽታዎች፡ ብርሃን እና ጨለማ
በህይወት ጉዟችን ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር እንገናኛለን። ከእነሱ መካከል ህይወታችንን የሚያበሩልን አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የፀሐይን ብርሃን ከእኛ ለመጋረድ እንደሚጥሩ ጥቁር ደመናዎች ናቸው። ጓደኝነታቸው በአዎንታዊ ስሜታቸው ምክንያት ሙቀትን ፣ ደስታን ፣ ምስጋናን የሚያጎናፅፉን እና ሁሉን ቻይ ወደሆነው አሏህ እንድንቀርብ የሚያደርጉን ሰዎች አሉ። እነዚህ የልብ ወዳጆች የእምነት ብርሃናችንን የሚያደምቁ ናቸው።
በተቃራኒው ደግሞ የህይወት ብርሃናችንን ለመጋረድ እንደሚጥሩ ጥቁር ደመናዎች የሆኑ ሰዎች አሉ። በህይወታችን ፣ በጌታችን እና በሃይማኖታችን ላይ አሉታዊ ስሜቶችን የሚዘሩ፤ ከእዝነቱ ነብይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መመሪያ ሊያርቁን የሚሞክሩ ናቸው። የእነሱ ወዳጅነት ከፈጣሪ እንዳያርቀን ሁሌም ልንሰጋ ይገባል።
ጓደኛን መምረጥ ለምን ወሳኝ ሆነ?
ኢስላም ጓደኝነትን እንደ ተራ ማህበራዊ ግንኙነት አድርጎ አይመለከተውም። ይልቁንም የእምነታችንና የመጨረሻ እጣ ፈንታችን መለኪያ አድርጎ ያስቀምጠዋል። የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ሲያረጋግጡ እንዲህ ብለዋል፡-
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚ)
“ሰው በጓደኛው ሃይማኖት (መንገድ) ላይ ነው፤ ስለዚህ አንዳችሁ ማንን እንደሚወዳጅ ይመልከት።”
ይህ ማለት የምንመርጠው ጥሩ ጓደኛ የዓቂዳችን፣ የስነ-ምግባራችንና የአኗኗራችን መስታወት ይሆናል ማለት ነው።
የመልካም ጓደኛ መገለጫዎች
ሁሌም ልንቀርባቸውና ልንወዳጃቸው የሚገቡን ጓደኞች የሚከተሉት ባህሪያት አሏቸው፡-
- አላህን ያስታውሱናል፡ በንግግራቸውም ሆነ በተግባራቸው ዘወትር ፈጣሪን ያስታውሳሉ።
- በመልካም ነገር ያግዙናል፡ መልካም ሥራዎችን እንድንሠራ ያበረታታሉ ፣ ይተባበራሉ።
- ከጎናችን ይቆማሉ፡ በክፉም በደጉም ከጎናችን በመሆን ያጸናሉ።
- እሴቶቻችነን ያከብራሉ፡ ኢስላማዊ እሴቶቻችነን ከፍ እንድናደርግና በህይወታችን ውስጥ ትክክለኛውን አቋም እንድንይዝ ያግዙናል።
ልንርቃቸው የሚገቡ ጓደኞች
በተመሳሳይ መልኩ ከእነዚህ አይነት ሰዎች መራቅ አለብን፡-
- የነፍስን ውበት ከሚያበላሹ፡ በሀሜት ፣ በውሸትና በሌሎች መጥፎ ድርጊቶች የልባችንን ንጽህና ከሚያቆሽሹ።
- አላህን ከማስታወስ ከሚያዘናጉ፡ ወደ ከንቱ ጨዋታዎችና የዱንያ ፍቅር ብቻ ከሚጣሩ።
- አሉታዊነትን ከሚዘሩ፡ በሁሉም ነገር ላይ ተስፋ አስቆራጭ እና አሉታዊ አመለካከት ካላቸው።
ልቦች እርጋታን እና ሰላምን የሚያገኙት አላህን በማውሳት መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ረዕድ 13፡28)
“አዋጅ! በእርግጥ አሏህን በማውሳት ልቦች ይረጋጋሉ።”
የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ጓደኝነት ምሳሌ ፡ የሽቶ ሻጩና የወናፍ ነፊው ታሪክ
የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የመልካም እና የመጥፎ ጓደኛን ልዩነት ከዓይነ ህሊናችን የማይጠፋ ድንቅ ምሳሌ አስቀምጠውልናል፡-
የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ እና ሙስሊም)
“የመልካም ጓደኛ እና የመጥፎ ጓደኛ ምሳሌ ልክ እንደ ሽቶ ሻጭ እና የብረት ቀጥቃጭ ወናፍ ነፊ ነው፡፡ ሽቶ ሻጩ ወይ በነፃ ይሰጥሃል ወይ ደግሞ ከእሱ ትገዛለህ ወይም ደግሞ ከእሱ መልካም መአዛ (ጠረን) ታገኛለህ። ብረት ቀጥቃጭ ወናፍ ነፊው ግን ልብስህን ያቃጥልብሃል ወይም ደግሞ መጥፎ ጠረን ታገኛለህ።”
ማጠቃለያ
መልካም ጓደኝነት በህይወታችን ላይ የምንወስነው ትልቅ ውሳኔ ነው። የምንመርጣቸው ወዳጆች ወይ እንደ ሽቶ ሻጩ ህይወታችንን በመልካም መዓዛ ይሞሉታል ወይም እንደ ወናፍ ነፊው የእምነታችንን ልብስ ያቃጥሉታል።
ስለዚህ ወደ ጀነት በሚወስደው መንገድ ላይ አጋዥ የሚሆኑንን ፣ አላህን የሚያስታውሱንና ለመልካም ነገር የሚያነሳሱን ጓደኞች በጥንቃቄ እንምረጥ። የህይወት ጉዟችነን ከማን ጋር እንደምንጓዝ ዛሬ መወሰን የነገ ማንነታችንን ይቀርጻል።
የእርስዎ የጓደኝነት ተሞክሮ ምን ይመስላል? መልካም ጓደኞች በህይወትዎ ላይ ያመጡትን በጎ ተጽዕኖ በአስተያየት መስጫው ላይ ያካፍሉን።
Share