ለምን ይሆን ሶላት የማንሰግደው?

Author picture
ለምን ይሆን ሶላት የማንሰግደው? ሶላት ከአሏህ ጋር ያለንን ትስስር ወይም ግንኙንነት የምናጠነክርበት ፣ ለኒዕማዎቹ ሁሉ የምናመሰግንበትና ልቅናውን የምናወሳበት ነው፡፡
ለምን ይሆን ሶላት የማንሰግደው?

ለምን ይሆን ሶላት የማንሰግደው? በአሏህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።

ሶላት ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ከአሏህ (ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ትስስር ወይም ግንኙንነት የምናጠነክርበት ፣ ለኒዕማዎቹ ሁሉ የምናመሰግንበትና ልቅናውን የምናወሳበት ቢሆንም ብዙ ሙስሊሞች ግን አይሰግዱም።

አካላችን ምግብና ውሃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ነፍሳችነም መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያስፈልገው ራሳችነን በአምልኮት ተግባራት ልናንፅ ይገባል። ከነዚህ የአምልኮት ተግባራት መካከል አንደኛውና ወሳኙ የሆኑ ነው ደግሞ ሶላት ነው።

በቡኻሪና ሙስሊም በተዘገበው ሐዲስ መሠረት ረሱል (ሰ.ዐ.ወ): አሏህን የሚያወሳና የሚያወሳ ሰው ንፅፅሩ ልክ ህያው እንደሆነ (በህይወት እንዳለ ሰው) እና በሙት ይመሰላል (ልክ እንደሞተ ሰው ነው) ብለዋል።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አንፋል 8:24)

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! መልዕክተኛው ህያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ ለአሏህና ለመልዕክተኛው ታዘዙ። አሏህም በሰውየውና በልቡ መካከል የሚጋርድ መሆኑን ወደ እርሱም የምትሰበሰቡ መሆናችሁን እወቁ።” 

ሶላት ከአሏህ ጋር በቀጥታ የምንገናኝበት ነው 

አንድ ሰው ወደ ጌታው በጣም የበለጠ የሚቀርበው ሱጁድ ላይ በሆነ ጊዜ ነው። የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ): ከናንተ መካከከል አንዳችሁ ለሶላት በቆመ ጊዜ ከአሏህ ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል።

የእስልምና ምሶሶ

ሶላት በሙስሊሞች ህይወት ውስጥ ግዴታ የሆነ የዘወትር ተግባር ሲሆን ከ5ቱ የእስልምና ምሶሶዎች ውስጥ ሁለተኛውና ወሳኙ የአምልኮት ተግባር ነው።

በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሁነን ቢሆን እንኳ ቢያንስ በቀን አምስት ጊዜ ልንሰግድ ይገባል። እነዚያ ብርቅየ ሶሃቦች ጦርነት ላይ ሁነው በነበረ ጊዜ እንኳ አሏህ ከሶላት ነፃናችሁ አልነበረም ያላቸው። ይልቁንም እንዲህ ሲል ነበር ያዘዛቸው፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ 2:238-239)

“ሶላቶቻችሁን ተጠባበቁ በተለይ የመካከለኛይቱ ሶላት (አስር ሶላትን)። ታዛዦች ሁናችሁም ለአሏህ ቁሙ። ብትፈሩም እግረኞች ወይም ጋላቢዎች ሆናችሁ ስገዱ።”

ታዲያ እነዚያ ብርቅየ ሶሃቦች የጦርሜዳ ላይ ሁነው ስገዱ ከተባሉ እኛስ በሰላም ጊዜ እንዴት ብላችሁ ስገዱነው የምንባለው?

ስኬት ያለው ሶላት ላይ ነው 

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ): የሰው ልጅ በዕለተ ትንሳኤ ከስራዎቹ መካከል በመጀመሪያ የሚጠየቀው ስለ ሶላት ነው። ሶላቱ ከተስተካከለ ይሳካለታል። ሶላቱ ያልተሟላ ከሆነ በዕጦት ይሰቃያል (ከከሳሪዎች ይሆናል)፤ ይዋረዳልም ብለዋል።

ሶላት የመጥፎ ነገሮች መከላከያ ጋሻ ነው 

የአሏህን እርዳታ ሳንሻ ከወንጀል ተግባራትቶች ልንርቅ አንችልም። እንዲሁም ለአሏህ ካለን ፋራቻ ፣ ውዴታና ታዛዥነት የተነሳ ሶላቶቻችነን በወቅቱና በሁሹእ የምንሰግድ ከሆነ ሃራም ነገሮችን አንፈፅምም።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አንከቡት 29:45)

“ከመፅሐፉ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ። ሶላት ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ሁሉ ትከለቀክላለችና።”

ሶላት መንፈሳችነን ያበለፅጋል

መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችነን በማርካት ሰላምና ደስታ እንዲሁም መረጋጋትን ያስገኛል። አሏህ በቁርአኑ በሱረቱል አልረዕድ አንቀፅ 28 ላይ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ረዕድ 13:28)

“እነዚያ ያመኑ ልቦቻቸው አሏህን በማውሳት የሚረኩ (የሚረጋጉ) ናቸው። ንቁ! አሏህን በማውሳት ልቦች ይረጋጋሉና።” 

ሶላት ሃጢያቶቻችነን ያብሳል

እንደሚታወቀው በዚህ ውስብስብ አለም ውስጥ ወንጀል ከመፈፀም የታቀበ ንፁህ የሆነ ሰው የለም። ደረጃው ይለያያል እንጅ ሁሉም የአደም ልጅ ወንጀል ይሰራል።

ከሰው ልጅ ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም አይደል የሚባለው። ሆኖም አሏህ (ሱ.ወ.ተ) በሶላት ጎዳና ወንጀላችነን የምናሳብስበትን መንገድ አስገኘን። አሏህ በቁርአኑ በሱረቱ ሁድ አንቀፅ 114 ላይ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ሑድ 11:114)

“ሶላትንም በቀን በሁለቱ ጫፎች ፣ ከሌሊትም ክፍሎች ፈፅም በእርግጥ መልካም ስራዎች ሃጢያቶችን ያስወግዳልና። ይህ ለተገሳጮች ግሳፄ ነው።”

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ): ለሶሃቦቻቸው እንዲህ ባሉ ጊዜ ምርጥ ምሳሌ ሰተው ነበር። ከእናንተ መካከል አንዳችሁ በቀን አምስት ጊዜ የሚታጠብበት የሆነ በበራፉ በኩል የሚያልፍ ወንዝ ቢኖረው በሱ ላይ ቆሻሻ ይቀራልን? አሉ። እነርሱም አይቀርም አሉ። እናም የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ): ልክ እንደዚሁ አሏህ በአምስት አውቃ ሶላቶች ሃጢያትን ያብሳል ሲሉ መለሱ።

ከአሏህ (ሱ.ወ.ተ) ጋር ያለንን ግኑኝነት ባጠነከርን ቁጥር አሏህ በማንኛውም ነገር ያግዘናል፤ የበለጠም ወደ እሱ ያቀርበናል፤ ችግሮቻችነንም ይፈታልናል።

አሏሁ አዘወጀል በቅዱስቃሉ በሱረቱል በቀራ አንቀፅ 153 ላይ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ 2:153)

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትዕግስትና በሶላት እርዳታን ሻቱ በእርግጥ አሏህ ከታጋሾች ጋር ነው።”

ሙስሊሞችን አንድ ያደርጋል

የጀመአ ሶላት ለብቻችን ከምንሰግደው በ25 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በመካከላችን ወንድማማችነት ፣ እኩልነት እና መተናነስ እንዲያብብ ያደርጋል።

ለሶላት በቆምን ጊዜ ዘር ፣ ብሔር ፣ ቀለም ፣ ጎሳ ወ.ዘ.ተ ሳይለያየን አንድ አካል ሁነን ትከሻ ለትከሻ ፣ እግር ለእግር ገጥመን ለአምላካችን አሏህ እናጎበድዳለን።

ሶላትን መተው እና መዘዙ

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ኢንፊጧር 82:6)

“አንተ ሰው ሆይ! በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ?”

የመኖራችን ሚስጥር፤ የመፈጠራችን አላማ አሏህን በብቸኝነት መገዛት ሆኖ ያለ እኛ ግን ስሜታችነን በመከተል አምላካችነን አመፅነው።

አሁን መስገድ አለብኝ ከማለት ይልቅ ነገ እሰግዳለሁ ማለትን ስንቅ አድርገን ያዝን። ነገ በህይወት ስለመኖራችን ዋስትናችን ምንድ ነው?

ውድ እህት ወንድሞቼ ሆይ! ቆም ብለን እናስብ እባካችሁ! እስኪ በሚከተለው የቁርአን አያ ልብ ብለን እናስተንትን። አሏህ (ሱ.ወ.ተ) በቁርአኑ በሱረቱል መርየም አንቀፅ 59 ላይ እንዲህ ይላል፦

አል-ቁርአን

(ሱረቱል መርየም 19:59)

“ከእነሱም በኋላ ሶላትን የተው ፍላጎቶቻቸውንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች(ትውልዶች) ተተኩ። በእርግጥ የጀሃነምን ሸለቆ ያገኛሉ።”

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ሙደሲር 74:42-43)

“በሰቀር ውስጥ (በጀሃነም ውስጥ) እንድትገቡ ያደረጋችሁ ምንድነው? ይባላሉ። እነሱም ከሰጋጆች አልነበርንም ይላሉ።”

አሏሁ አዘወጀል ብዙ ዕልቆቢስ የሆኑ ኒዕማዎችን በዙርያችን ሰጠን፤ አስታውሱኝ አስታውሳችኋለሁና አለን፤ ለኔም አመስግኑ አትክዱኝም ሲለን እኛ ግን ፊታችነን ዘወር አድርገን ሶላትን ተውን፤ የአሏህን በረካዎች በልተን እንዳልበላን ሆን። በእርግጥም ይህን በማድረጋችን ከአሏህ ጋር ያለንን ግኑኝነት አቋረጥን።

ውድ እህት ወንድሞቼ እናስተውል! እኛ ስለሰገድን ስላልሰገድን ፣ ስላመሰገነው ስላላመሰገነው አሏህ የሚጎልበት ነገር የለም። እኛ የምንጎዳ ብንሆን እንጅ።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ሙልክ 67:23)

“እሱ ያ የፈጠራችሁ ለእናንተም መስሚያና ማያዎችን ልቦችንም ያደረገላችሁ ነው። ጥቂትንም አታመሰግኑም በላቸው።”  

ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ለረጅም ጊዜ ለሶላት በመቆም እግራቸው ያብጥ ነበር። አንዴ ስለዚህ ነገር ተጠይቀው “ለጌታየ አመስጋኝ ባርያ መሆን የለብኝምን?” ሲሉ መለሱ። እኛ ግን አይደለም ቂያመለይል የግዴታ ሶላቶቻችን እንኳ ከብደውናል። እስኪ በልቦቻችን ውስጥ ያለውን ነገር እንፈትሽ!

ደካሞች እየሆን ነው

የሰማያትና የምድር እንዱሁም የፍርዱ ቀን ባለቤት ለሆነው አምላካችን አሏህ ሶላትን ምን ብለን ተውን ነው የምንለው? አሏህ (ሱ.ወ.ተ) 24 ሰዓቶችን ሰቶን ባረባ ነገር ብዙ ጊዜያችነን እያጠፋን ታዲያ ለሶላት እንዴት 15 ደቂቃ አጣንለት?

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፡ በትንሳኤ ቀን የአደም ልጅ ስለአምስት ጉዳዮች ሳይጠየቅ እግሮቹን አያንቀሳቅስም። ህይወቱን በምን እንዳሳለፈ ፣ ምን በመስራት ወጣትነቱን እንዳሳለፈ ፣ ሃብት ንብረቱን የት እንዳገኘውና በምንላይ እንዳወጣው እንዲሁም ባወቀው ነገር ላይ ምን እንደሰራ ሳይጠየቅ ብለዋል።

ሌላው ማወቅ ያለብን ነገር ብዙ ኡለማዎች ሶላትን የተወ ሰው ከሐዲ ነው ሲሉ ፈትዋዎችን ሰተዋል። ይህም የሚከተለውን ሐዲስ በመጥቀስ ነው።

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ): በከሐዲዎችና በእኛ መካከል የሚለየን ሶላት ነው። እሷን ችላ ያለ በእርግጥ ካደ ብለዋል።

ሶላት ለመተዋችን የምናቀርባቸው የተለመዱ ምክኒያቶች

ጥናቴ /ስራየ/ ተጨናንቂያለሁ

ብዙ የሚያረይረብ ነገሮችን እየሰራን፤ ከአንድ ሰዓት በላይ በወሬ እየጨረስን፤ ከአንድ ሰዓት በላይ ሶሻል ሚድያዎችን እየተጠቀምን እንዲሁም ለአንድ ሰዓት ያህል ቻት እያደረግን ለሶላት ጊዜ አጣን? ከሶላት በላይ ጥናታችነን እና ስራችነን እንዴት እናስቀድማለን?

እህት ወንድሞቼ ከማንኛውም ስራ በላይ ሶላትን ነው ማስቀደም ያለብን። ያኔ ሶላታችን ከማንኛውም ነገር በላይ ባስቀደምን ጊዜ አሏህ ሰዓታችነን ይባርክልናል፤ በጥናታችንም ሆነ በስራችን ብቁና ስኬታማ ያደርገናል።

አላርም ስላልቀጠርኩ ነው

ኒያችነን በማስተካከል በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) መንገድ እንተኛ።

ልቤ ንፁህ ነው

ልባችን የፈለገ ያህል ንፁህ ቢሆንም አሏህ እንድንሰግድ ይፈልጋል። ምክኒያቱም የተፈጠርንበት አላማ ይህነውና።

በእርግጥ ተግባራችን ወይም ስራችን በልባችን ውስጥ ላለው ነገር ነፀብራቅ ነው። ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በላይም ንፁህ ልብ ያለው የለም።

ብዙ ሃጢያት ወይም ወንጀል እየሰራሁ ነው

በአሏህ ፈቃድ ሶላታችን ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ሁሉ ይከለክለናል። ዋናው ከኛ የሚጠበቀው ከልብ በመነጨና ቅን በሆነ ተውባ ወደ አሏህ መመለስ እንዲሁም ሶላት ከመጥፎ ነገር የሚከለክል መሆኑን ከልባችን ማመንናና ሶላቶቻችንን በወቅቱ ከኹሹእ ጋር መስገድ ነው።

0%
3
Question report close icon

Report a question

You cannot submit an empty report. Please add some details.
Question report loader icon
Created by Ahmed Yesuf

ሶላት

ጥያቄና መልስ፡ የጀመአ ሶላት (የህብረት ስግደት)

‹‹ሶላቱል ጀመአ (የህብረት ስግደት)›› የሚለው ትምህርት ፈተና 6 ጥያቄዎችን ይዟል። ፈተናውን ለማለፍ 5 ጥያቄዎችን በትክክል መመለስ አለባችሁ።

1 / 6

Bookmark question icon

1 የጀመአ ሶላት ሊባል የሚችለው በትንሹ ስንት ሰዎች ሲታደሙ ነው?

2 / 6

Bookmark question icon

2 ከኢማሙ ጋር አብሮ የሚሰግደው አንድ ሰው ብቻ ከሆነ የሰውየው አቋቋም ምን መሆን አለበት?

3 / 6

Bookmark question icon

3 እውነት ወይም ሐሰት፡ ኢማሙ በሩኩዕ ሁኔታ ላይ ሆኖ ሳላ ሰጋጁ ጀመአውን ከተቀላቀለ እንደ አንድ ሙሉ ረከአ ይቆጠራል፡፡

4 / 6

Bookmark question icon

4 እውነት ወይም ሐሰት፡ ኢማሙ (ጀመአውን የሚመራው) ሁልጊዜም በእድሜ ከፍ ያለ ነው፡፡

5 / 6

Bookmark question icon

5 ጀመአውን ዘግይየት ብሎ የተቀላቀለ ሰው ማድረግ ያለበት ምንድን ነው?

6 / 6

Bookmark question icon

6 ከኢማሙ ጀርባ የሚሰግድ ሰው ኢማሙን መከተል ያለበት በምን አግባብ ነው?

የተሳታፊ መረጃ

Your score is

The average score is 13%

0%

ለሰጡን ሀሳብ አስተያየት እናመሰግናለን!

Related posts

ሲዋክ እና ጥቅሞቹ

ሲዋክ እና ጥቅሞቹ

ኢስላም ንፅህናን የእምነቱ ግማሽ አካል ያደረገ ብቸኛ መለኮታዊ ሃይማኖት ነው። ሲዋክ ማለት ጥርስንና አፍን በእንጨት መፋቂያና መሰል ነገራት ከመጥፎ ጠረንና ቅሪቶች ማጽዳት ማለት ነው፡፡

Read More »
ሱጁድ

ሱጁድ

ሱጁድ ማለት በሶላት ውስጥ የመስገጃ ቦታ ላይ ግንባርን የመድፋት ተግባር ነው። ይህ የሚፈፀመው ግንባርን እና አፍንጫን ወለሉ ላይ በማስነካት ፣ መዳፎችን ወለሉ ላይ በማሳረፍ ፣

Read More »
ኢቃም

ኢቃም

ኢቃማ ከፈርድ (ግዴታ) የጀመአ ሶላት መጀመሪያ ላይ የሚባል መነባነብ ነው። አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) “የአዛን ቃላት ሁለት ጊዜ እና የኢቃም ቃላትን በተናጠል አንድ ጊዜ ብቻ

Read More »
ረከአ

ረከአ

እያንዳንዱ ሶላት የአንድ ወይም የሁለት ፣ የሶስት ወይም የአራት ረከአ ህብር ነው። እያንዳንዱ ረከአ አቋቋሞች ወይም ቅርፆች አሉት፤ መጀመሪያ መቆም ፣ ከዛም መዳፎችን ጉልበት ላይ

Read More »

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share