በችግር ጓዶች ተፅናና

Author picture
በችግር ጓዶች ተፅናና! ብቻዎትን አይደለም። ይህ ፅሁፍ መከራ የሁሉም የሰው ልጆች ተሞክሮ እንደሆነ ፣ ነብያት እና ደጋጎችን ጨምሮ ሁሉም ፈተና እንደገጠማቸው በማሳየት እንዴት በችግር ጊዜ መፅናናት እንደምትችሉ ያሳያል።

በችግር ጓዶች ተፅናና! እስቲ አንዴ ወደ ቀኝህና ወደ ግራህ ዘወርብለህ ተመልከት። በችግር የተፈተነ ወይም በጉዳት የሚሰቃይ እንጂ ሌላ ይታይሃልን?

በየጓዳው የሚያለቅስ፤ በየጉንጩም ላይ እንባ አይጠፋም።

ብዙ ተጐጅዎችና ብዙ ታጋሾችም አሉ። አንተ ብቻ አይደለህም የምትሰቃየው እንዲያውም ከሌሎቹ አንፃር ያንተ ስቃይ እጅግ የቀለለ ነው።

ስንት ከአልጋው ላይ ተጋድሞ ለዓመታት ሳይነሳ ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ እየተገላበጠ ከህመሙ የሚሰቃይ ፣ በቁስሉ የሚጮህ አለ።

  • ስንትስ እስረኛ አለ በዓይኑ ፀሀይን ሳያይ እስርቤት ውስጥ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ?
  • ስንቶቹስ ወንዶችና ሴቶች አሉ የአብራካቸውን ክፋዩች በጋለ እድሜያቸው ያጧቸው?

ስንትና ስንት ችግረኛ ፣ ብድር ያለበት ፣ ጉዳተኛ እና ከስቃይ የሚማቅቅም አለ። በነዚህ የምትፅናናበትና ይህች ህይወት የአማኞች እስርቤት እና የችግሮችና የጉዳቶች መንደር መሆኗንም የምታውቅበት ጊዜው አሁን ነው።

ቤተመንግስታት በነዋሪዎቻቸው ደምቀው እንዳላነጉ ባዶዋቸውን ያመሻሉ።

ቤተሰቡ ተሟልቷል ፣ የአካልም ጤንነት ይጠበቃል ፣ ሀብትም ተትረፍርፏል ፣ ልጆች በዝተዋል ሲባል በጥቂት ቀናት ውስጥ ድህነት ፣ ሞት ፣ መለያያትና በሽታዎች ተጠራርተው ይመጣሉ።

አል-ቁርአን

ሱረቱ ኢብራሂም 14:45

«በነሱም እንዴት እንደሰራንባቸው ለናንተ ተገለፀላቹ ፤ ለናንተም ምሳሌዎችን ገለፅንላችሁ።»

ስለዚህ ጠንክር ብለህ ችግሮችን ማለፍ ይጠበቅበሃል። የደረሰብህንም ጉዳት በዙሪያህ ካሉትና ካንተ በፊት ኖረው ካለፉት ሰዎች ጉዳት ጋር ማነፃፀርም ይኖርብሃል።

ያኔ ከነዚህ ሰዎች አንፃር ጤነኛ መሄንህን ትረዳለህ። ቀላል ጉዳቶችን እንጂ እንዳልተጎዳህም ትገነዘባለህ።

ስለዚህ ስለዋለልህ ውለታ አሏህን አመስግነው። ጉዳት እንዳያደርስብህ ስላስቀረልህም ነገር ሁሉ አወድሰው።

የወሰደብህን ነገር በተሻለ እንዲተካልህም ከጅለው። በዙሪያህ ባሉትም ተፅናና።

በዚህም ታላቁ አርአያህ መልእክተኛው {ሰ.ዐ.ወ} ናቸው።

በራሳቸው ላይ የእንግዴ ልጅ ተደርጎባቸው፤ እግሮቻቸው እስኪደሙ ተመተው፤ ፊታቸውን ተፈንክተው፤ የዛፍ ቅጠል እስኪበሉ ድረስ ሸለቆ ውስጥ ታግደው፤ ከመካ ተባረው፤ የፊት ጥርሶቻቸው ተሰብረው፤ የተከበረችውን ባለቤታቸውን (አኢሻ) ክብር አጉድፈውባቸው፤ ሰባ ያህል ጓደኞቻቸው ተገድለው፤ እሳቸው በህይወት ሳሉ ወንድ ልጃቸውና አብዛኛዎቹ ሴት ልጆቻቸው ሞተውባቸው፤ ከረሃብ የተነሳ የሚበሉትን አጥተው ሆዳቸውን በድንጋይ አስረው ገጣሚ ፣ ድግምተኛ ፣ ጠንቋይ ፣ እብድና ውሸታም ተብለው አልፈዋል።

ይህም ታላቅ መከራና አምሳያ የሌለው ፈተና ነበር። ከሳቸውም በፊት ዘከሪያ ተገድሏል፤ የሕያም ታርዷል፤ ነብዩ ሙሳ ታግዷል፤ ነብዩ ኢብራሂም (የአሏህ ወዳጅ) እሳት ላይ ተጥለዋል።

ሁሉም ታላላቅ ሰዎች በተመሳሳይ ጐዳና ላይ አልፈዋል። ኡመር ኢብን አል-ኸጧብ (ረ.ዐ) በደማቸው ተጥለቅልቀዋል፤ ኡስማን ኢብን አፋን (ረ.ዐ) ተገድለዋል ፤ አሊ ኢብን አቢ ጧሊብ (ረ.ዐ) ተወግተዋል፤ የኢስላም ምሁራን ጀርባዎቻቸውን ተገርፈዋል፤ አማኞች ታስረዋል፤ የአሏህ ደጋግ ባሮችም ተሰቃይተዋል።

አል-ቁርአን

ሱረቱል በቀራ 2:214

«በእውነቱ የነዚያ ከበፊታችሁ ያለፉት ምዕመናን መከራ ቢጤ ሳይመጣባችሁ ገነትን ልትገነቡ ታስባላችሁ? መልክተኛውና እነዚያ ከሱ ጋር ያመኑት የአሏህ እርዳታ መቼ ነው? እስከሚሉ ድረስ መከራና ጉዳት ነካቻቸው ተርበደበዱም።»

Related posts

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share