የሰው ልጅ ሆይ ከረሃብ በኃላ ጥጋብ አለ ፣ ከጥማት በኃላም እርካታ አለ ፣ ከእንቅልፍ እጦት በኃላም እንቅልፍና ከበሽታ በኃላ ጤና አለ።
የጠፋው ይገኛል ፤ የጠመመውም ይቃናል ፤ በአይን የተበላውም ይድናል ፤ ጨለማውም ይገፋል።
አል-ቁርአን
{ሱረቱ ደህር 76:9}
«አሏህም ድልን ወይም ከርሱ ዘንድ የኾነን ነገር እንዲያመጣ ይከጅላል።»
በተራሮች ላይ እና በየሸለቆዎቹ የሚያሳድደው ንጋት እንደሚመጣ ሌሊትን አብስረው ፣ የተጨነቀውንም ሰው በዓይን ጨረፍታ እና በብርሃን ፍጥነት የሚደርስ ድንገተኛ መፍትሄ እንደሚገኝ አብስረው ፤ አደጋ የደረሰበትንም ሰው ድብቅ መዳኛ እነደሚያገኝም አብስረው።
በረሃው እየሰፋ መሆኑን ካየህ አረንጏዴ መስኮች እንደሚከተሉ እወቅ። ገመድም በኃይል ከተጎተተ እንደሚበጠስ እወቅ።
እምባን ተከትሎ ፈገግታ አለ ፤ ፍርሃትን ተከትሎ አማን ፣ ድንጋጤን ተከትሎ መረጋጋት አለ። ወደ አሏህ አንድነት የሚጣራውን ነብዩ ኢብራሂም እሳት ልታቃጥለው አልቻለችም ምክኒያቱም መለኮታዊው እንክብካቤ እሳትን «ቀዝቃዛና ሰላም ሁኚለት» የሚለውን የእዝነት መስኮት ከፍታለታለችና።
ባህሩም ነብዩ ሙሳን አላሰመጠችውም ምክኒያቱም እውነተኛውና ኃያሉ ድምፅ «ጌታዮ አብሮኝ አለ ይረዳኛልም» ብሏልና።
ነብዩ ሙሐመድ [ሰ.ዐ.ወ] ዋሻ ውስጥ ጓደኛቸውን ሲያፅናኑ «አሏህ ከኛጋር ነው» አሉ። በዚያም አማንን እርጋታንና በመጨረሻም ድልን አገኙ።
የአስቸጋሪ ጊዜያቸውና የነባራዊ ሁኔታቸው ባሮች ሁሌም የሚታያቸው ጥበት ፣ ችግር እና እድለቢስነታቸው ብቻ ነው።
ምክኒያቱም ከቤቱ መግቢያ በር እና መስኮት ውጭ አሻግረው አይመለከቱም። ዓይኖቻቸውን ከግርዶው ጀርባ አሳልፈው ይመለከቱ፤ አስተሳሰባቸውንም ከአጥሩ ጀርባ ያሻግሩ።
ራስህን አታጨናንቅ። ያለህበት መከራ እስከ መጨረሻው አይቀጥልምና ከኢባዳዎች (ከአምልኮዎች) በላጩ የአሏህን መፍትሄ መጠበቅ ነው።
ቀናት ይገለባበጣሉ፤ ዓመታትም ይለዋወጣሉ። የሩቅ ሚስጥሩም ድብቅ ነው።
ጥበበኛውም ጌታ በየቀኑ በተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ነው ፤ ምናልባትም ከዚያ ብኃላ ሌላን ነገር ሊያስከትል ይችላል፤ መከራንም ተከትሎ ምቾት ይመጣል።
Share