ተሐጁድ የሶላቱ ተሃጁድ አህፅሮት ሲሆን ትርጉሙም የሌሊት ሶላት ማለት ነው። የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የዘወትር ተግባር ነው። የተረጋገጠ የነብዩ ሱና ነው። በአሏህ መንገድ ነፍሳችንን የምናጠራበት ፣ የአሏህ ፍራቻ እና ፅናት የምናበለፅግበት ጥሩ መንገድ ነው።

ምንም እንኳ ተሐጁድ የነብዩ ሱና ተግባር ቢሆንም ምዕመናን እንዲያዘወትሩት ያበረታቱ ነበር።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(በአል-ሂከም ተዘግቧል)
“የሌሊት ስግደት ተከታተሉ ከእናንተ በፊት የነበሩ ደግ ህዝቦች ባህሪ ነውና። ወደ ጌታችሁ ያቀርባችኋል፤ ወንጀላችሁን ያብሳል ፣ ከመጥፎ ስራ ይከለክላችኋል።”
እንዲህም ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ሙስሊም)
“ከፈርድ (ግዴታ) ሶላት ቀጥሎ በላጩ ስግደት የሌሊት ስግደት ነው።”
ምንም እንኳ አሏህ ያለፈውን እና የሚመጣውን ወንጀላቸውን የሰረየላቸው ቢሆንም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እግራቸው እስኪያብጥ ድረስ ረዘም ላለ ጊዜ በተሃጁድ ይቆሙ ነበር።
የተሃጁድ ረከአ ቢያንስ ሁለት ረከአ ቢበዛ ከአንድ ተስሊም (አሰላሙ አለይኩም ማለት ከሶላቱ መጨረሻ ላይ በቀኝ እና በግራ) ጋር አድርገው ይሰግዱ ነበር። ዊትርን ጨምሮ ከአስራ ሁለት ረከአዎች የበለጠ ሰግደው አያውቁም።
የተሐጁድ በላጩ ጊዜ ወደ ሌሊቱ መጨረሻ የቀረበው ነው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
“የተባረከውና የተላቀው ጌታችን ሁልጊዜ ሌሊት ላይ ወደ ዱንያ ሰማይ ይመጣል። ማነው የሚጠራኝ (የሚለምነኝ) የምመልስለት? ማነው የሚጠይቀኝ የምሰጠው? ምህረቴን የሚፈልግ ማነው የምምረው? ይላል።”
የተሐጁድ ሶላት የሚሰግዱትን አሏህ አሞካሽቷል።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ሰጅዳ 32፡16-17)
ጎኖቻቸው ከምኝታቸው ይላቀቃል፤ ጌታቸውን በፍርሃት እና በተስፋ ይጣራሉ። ከሰጠኛቸውም ነገር ይለግሳሉ። ይሰሩት ለነበረው ምንዳ ለአይኖቻቸው መርጊያ የተደበቀላቸውን ፀጋ አንድትም ነፍስ አታውቅም።

ሶላት ፣ ዊትር እና ረከአ ተመልከቱ




Share