ለይለቱል ቀድር (የውሳኔው ወይም የድንጋጌው ምሽት) በመጨረሻው የረመዷን አስር ሌሊቶች ውስጥ በአንዱ ሌሊት ውስጥ የሚገኝ ነው።
ይህ ምሽት አሏህ ቁርአን ያወረደበት እና በጎ ስራዎችን ከሽህ ወራቶች ስራ በላይ በላጭ ያደረገበት ሌሊት ነው። አሏህ እንዲህ ይላል፡
አል-ቁርአን
(ሱረቱል ቀድር 97፡1-5)
በእርግጥ(ይህን ቁርአን) በቀደር ሌሊት አወረድነው። የቀደር (የድንጋጌው) ምሽት ምን እንደሆነ ምን አሳወቀህ? የቀደር ምሽት ከሽህ ወራቶች በላይ በላጭ ናት። በእሷ ላይ መልአክቶችና መንፈሱ በጌታቸው ፈቃድ ከድንጋጌዎቹ ሁሉ ጋር ይወርዳሉ። የፈጅር ጎህ እስኪቀድ ድረስም ሰላም ናት።

እንዲሁም ቅዱስ ቁርአን የተባረከች ሌሊት ሲል ገልፃታል።
አል-ቁርአን
(ሱረቱ ዱኻን 44፡3)
በተባረከች ሌሊት ውስጥ (ቁርአንን) አወረድነው።
የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ለይለቱል ቀድር ትሩፋቶች ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪና ሙስሊም)
”በለይለቱል ቀድር ምሽት አምኖበት እና የአሏህን ምንዳ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጎ ሶላትችን የሰገደ ሰው ያለፉ ወንጀሎቹ ሁሉ ይማሩለታል።”
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለይለቱል ቀድርን ይፈልጉ ነበር። ሶሃባዎቹም ይህን እንዲያደርጉ አዘዋል። በዚህ በተባረከ ወር ውስጥ ያሉ የመጨረሻዎቹን አስር ሌሊቶች በአምልኮ ያሳልፉ ዘንድ ቤተሰቦቻቸው ይቀሰቅሱ ነበር።
አኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈችው የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪ)
”የረመዷን የመጨረሻ አስር ሌሊቶች ውስጥ ለይለቱል ቀድርን ፈልጉ ብለዋ።”
እንዲህም ብላለች ”የረመዷን የመጨረሻ አስር ቀናት መጀመርን ተከትሎ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወገባቸውን ያጠብቁ ነበር። ሌሊቱን ሙሉ ነቅተው ያሳልፋሉ፤ ሶላት ይሰግዳሉ፤ ቤተሰቦቻቸውንም ይቀሰቅሱ (ያነቁ) ነበር።” (ቡኻሪ)




Share