ሲያም (ፆም) ማለት የአሏህን ውዴታ በመሻት ፀሐይ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ከምግብ ፣ ከመጠጥ እና ግብረስጋ ግኑኝነት ከመፈፀም መታቀብ ነው።

ፆም ልዩ የሆነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ተግባር ነው። የፆም ዋናው አላማ ተቅወሏህ (አሏህን መፍራት) ለማግኘት ነው። ቅዱስ ቁርአን እንደሚለው
አል-ቁርአን
(ሱረቱል በቀራ 2፡183)
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አሏህን ትፈሩ ዘንድ፤ ፆም ከእናንተ በፊት በነበሩ ህዝቦች ላይ እንደተደነገገው ሁሉ በእናንተም ላይ ተደነገገ።
ፆም ጥሩ ባህሪን እና ጠንካራ ስብዕናንን ለማነፅ ይረዳል። ለድሆች እና ለተቸገሩት ማዘንን ፣ መራራትን ያጎለብታል። ፆመኛ ሰው ሲርበው ድሆችን እና የተቸገሩትን ያስታውሳል። አሏህ በእሱ ላይ የዋለውን ሲሳይም ያስታውሳል።
ይህን ማስታወስ ደግሞ አሏህ በእሱ ላይ ላደረጋቸው እልቆቢስ ፀጋዎች አመስጋኝ እንዲሆን ያስችላል።

ፆም ትዕግስትን እና ቻይነትን ፣ ደግነትን እና መራራትን ያላብሳል። አካልንም ያጠነክራል። ለብዙ በሽታዎችም መድሃኒት ነው። የምግብ እንሽርሽሪት ስርአትን ያዝናናል፤ ያሳርፋል።
ለጤና ጠንቅ የሆኑ ቆሻሻዎችን ከአካል እንዲወገዱ ይረዳል። በአሁኑ ሰአት በምዕራቡ አለም ብዙ ሰዎች በመፆም መዳንን ይፈልጋሉ።
ከፆም ግዴታዎች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው መጥፎ እና የተጠሉ ነገሮችን ፣ ወንጀሎችን ሁሉ መራቅ እና መጠንቀቅ ነው።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)፡
“አንዳችሁ በፆማችሁ ጊዜ መጥፎ ቃልን (ንግግርን) አይጠቀም ወይም መጥፎ ምግባርን አይፈፅም። የሆነ ሰው ከተፋለመው ወይም ከሰደበው ‘እኔ ፆመኛ ነኝ! እኔ ፆመኛ ነኝ!’ ይበል።” ብለዋል። (ቡኻሪ እና ሙስሊም)
የሚከተሉት ተግባራት በፆም ቀን የሚወደዱ ናቸው።

- የሱሁር ምግብ መብላት፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) “የእኛን ፆም ከአህሉል ኪታብ (ከመጽሐፉ ሰዎች) ፆም የሚለየው የስሁር ምግብ መብላት ነው።” ብለዋ። (ሙስሊም)
- ፀሐይ እንደጠለቀች ወዲያውኑ ለማፍጠር/ ፆምን ለመፍታት መቻኮል
- ፆምን በተምር ወይም በውሃ መፍታት
- ባፈጠሩ ጊዜ ዱአ ማድረግ
የረመዷን ፆም አዕምሮው ጤናማ በሆነ ፣ ለአካለ መጠን በደረሰ ፣ በጉዞ ላይ ባልሆነ ፣ በሽተኛ ባልሆነ እና መፆም በሚችሉ ሙስሊሞች ላይ ሁሉ ግዴታ ነው። ሴቶች የወር አበባ ላይ እና የወሊድ ደም ላይ እስካልሆኑ ድረስ መፆም ይገደዳሉ።



Share