መቅድም
በእርግጥ ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው። እናመሰግነዋለን፤ እንለምነዋለን፤ ምህረትን እንሻዋለን፤ ከነፍሳችን ክፋት እና ከድርጊቶቻችን መጥፎ ውጤቶች በአላህ እንጠበቃለን። አላህ የመራውን ማንም አያሳስተውም፤ አላህ ያሳሳተው ደግሞ የሚመራው የለውም።
ከአላህ በስተቀር በእውነት ሊያመልኩት የሚገባ አምላክ የለም፤ ብቸኛ እና ተጋሪ ባላንጣ የሌለው መሆኑን እመሰክራለሁ፡፡ ሙሐመድም ባሪያው እና መልእክተኛው ናቸው ብዬ እመሰክራለሁ።
ይህ የአህለ ሱና ወልጀማአ እምነት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ያተኮረ አጭር ጽሑፍ ነው። ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው እና የታተመው ብዙ አንባቢዎች ፣ የእውቀት ተማሪዎች እና አማኝ ሙስሊሞች ስለ ሰለፎች [ስለ ቀደምት ጻድቃን የእስልምና አባቶችና ተከታዮቻቸው] እምነት መሠረታዊ ነገሮች እና ህጎች አጭርና ግልጽ ማብራሪያ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጻቸው ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው።
በተመሳሳይ ጊዜ በተቻለ መጠን ከሰለፎች ምሁራን በተወረሰው ሸሪዓ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉትን ቃላትን ሳንጨምር ሳንቀንስ ተጠቅመናል፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ውይይት በዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ ብዙውን ጊዜ አስፈላጊ ከሆኑ ዝርዝሮች ፣ ትርጓሜዎች ፣ ማስረጃዎች ፣ ግለሰቦች ፣ ጥቅሶች እና የግርጌ ማስታወሻዎች ነፃ ነው። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱን ዓላማ በአነስተኛ የኪስ መጽሐፍ ውስጥ በዚህ ጊዜ ማሳካት አልተቻለም።
አላህ ከፈቀደ! ይህ ሥራ ክፍተቶቹን ለመሙላት እና ተጨማሪ ነገር ለሚፈልጉ ሰዎች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በልዩ ባለሙያ ተጨማሪ ነገሮች ተካተውበት እንዲዘጋጅ እናደርጋለን።
ይህንን ሥራ ለክቡር ሼክ አብዱረህማን ኢብኑ ናስር አል-በራክ ፣ ዶክተር ሐምዛ ኢብኑ ሑሰይን አል-ፊዕር እና ዶክተር ሰፈር ኢብኑ አብዱረህማን አል-ሐዋሊ አቅርቤያለሁ። አላህ ምንዳቸውን ይክፈላቸው!
እያንዳንዳቸው የራሳቸውን አስተያየት ጨምረዋል። ይህንን ተግባር አላህ በእሱ ፊት ንጹህ እንዲያደርግልን እጠይቃለሁ፡፡
ለአለም ሁሉ ምህረት ተደርገው የተላኩትን ነቢዩ ሙሐመድን ፣ ቤተሰባቸውን ፣ ባልደረቦቻቸውን እና እሳቸውን የተከተሉትን ሁሉ በመላእክቱ መካከል እንዲጠቅስልን እለምነዋለሁ፡፡ ከማንኛውም ጉዳት ይጠብቃቸው፤ ይባርካቸው።
አቂዳ
በቋንቋ ደረጃ አቂዳ የሚለው ቃል “ማወቅ ፣ ማሰር ፣ አጥብቆ መቋጠር ፣ ማጠናከር እና መለጠፍ” ማለት ነው። በሊቃውንት ስምምነት ደግሞ አቂዳ የሚለው ቃል “ለማንኛውም ጥርጣሬ የማይጋለጥ ጽኑና የማያወላውል እምነት” ማለት ነው።
አቂዳ የእስልምና እምነት በሚከተሉት ላይ ጽኑና የማያወላውል እምነት (ኢማን) ማሳደርን ያመለክታል፡-
1 ተውሂድ ፣ ኢባዳ (አምልኮ) እና መታዘዝ ሁሉም ለሃያሉ አላህ ብቻ የተገባ ነው።
2) መላእክቱ
3) መጽሐፍቱ
4) መልእክተኞቹ
5) የመጨረሻው ቀን
6) የአላህ ውሳኔ (ቀደር)
7) ከቀደምት ህዝቦች ዘገባዎች ከተረጋገጡት የቀሩ ዓለም ጉዳዮች
8) ከእውቀት ወይም ከድርጊት ጋር የተያያዙ ሁሉም ፍጹማዊ ጉዳዮች።
ሰለፎች
ሰለፎች የመጀመሪያ ዘመን ላይ የነበሩ የሙስሊሙ ኡማ ናቸው፡፡ የነቢዩ ባልደረቦች ፣ ተከታዮቻቸው እና ከዚህ ኡማ የመጀመሪያዎቹ ሶስት የተመረጡ ትውልዶች መካከል የነበሩ ምሁራን ናቸው።
“ሰለፊ” የሚለው ስያሜ ከዚህ ኡማ በቀሩት ዘመናት እነሱን እና መንገዳቸውን የሚከተሉትን ሁሉ ያመለክታል።
አህለ ሱና ወልጀማአ
አህለ ሱና ወልጀማአ ማለት ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እና ባልደረቦቻቸው በነበሩበት መንገድ ላይ ያሉ ሁሉ ናቸው። “አህለ ሱና” የተባሉት የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱና በመከተላቸው እና በመተግበራቸው ነው።
“ጀማአ” የተባሉት በእውነት ላይ የተሰባሰቡ እና በሃይማኖቱ ውስጥ በቡድን ያልተከፈሉ በመሆናቸው ነው፡፡ በህጋዊ ገዥዎች ዙሪያ የተሰባሰቡና በእነሱ ላይ ያላመፁ ናቸው፡፡
እንዲሁም ሰለፎች በአንድ ድምፅ የተስማሙበትን ነገር ተከትለዋል። የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱና መንገድ የሚከተሉ በመሆናቸው “አህለል ሐዲስ” ፣ “አህለል አሳር” እና “አህለል ኢቲባዕ” በመባልም ይታወቃሉ። ይህ ማለት “የሐዲስ ሰዎች” ፣ “የተላለፉ ዘገባዎችን የሚከተሉ ሰዎች” እና “ነቢዩን የሚከተሉ ሰዎች” ማለት ነው፡፡
እነሱ በዚህ ዓለም “አሸናፊ ቡድን” ሲሆኑ በመጨረሻው ዓለም ደግሞ “የሚድነው ቡድን” ናቸው።
የአህለ ሱና ወልጀማአ እምነትን ለማግኘት እና ለማውጣት የሚጠቀሙበት ዘዴ፡-
- የእምነት (የአቂዳ) ምንጭ መሰረቱ የአላህ ቃል ቁርአን ፣ የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ትክክለኛ ሱና እና የጻድቃን ሰለፎች ስምምነት (ኢጅማዕ) ብቻ ነው።
- ትክክለኛ የሆኑትን የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱናዎች መቀበል ግዴታ ነው፡፡ ምንም እንኳን የተላለፈበት መንገድ አሐድ ወይም ላልተዋተር ቢሆንም ማለት ነው። ሙተዋተር ዘገባ ማለት አራት ሁኔታዎችን የሚያሟላ ነው፡-
ሀ) በተለምዶ በውሸት መሰብሰብ በማይቻል ሁኔታ ላይ እጅግ ብዙ ቁጥር ባላቸው አስተላላፊዎች የተዘገበ መሆኑ
ለ) እንዲህ ያለ ቁጥር በዘገባው ሰንሰለት ውስጥ በሙሉ መኖሩ
ሐ) ዘገባው መሰረቱ በተሰማ ወይም በታየ ነገር ላይ መሆኑ
መ) ዘገባው ለሚሰማው ሰው እውቀት የሚያስገኝ መሆን አለበት።
3) የአላህን ቃልና ሱና ለመረዳት መነሻ ነጥብ ትርጉማቸውን የሚያብራሩ ጽሑፎች (ኑሱስ) ፣ የጻድቃን ሰለፎች እና የምሁራን ግንዛቤ እና ጥበብ ነው።
ይህ በአረቦች ቋንቋ ትክክለኛ የሆነውን መከተል ያስፈልጋል። ሆኖም ከላይ የተረጋገጠውን ቋንቋ ብቻ ተንተርሶ መቃወም አይቻልም።
4) ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) የሃይማኖቱን መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ አብራርተዋል። ስለዚህ ማንም ሰው አዲስ ነገር ፈጥሮ ከሃይማኖቱ ነው ብሎ በመናገር አይፈቀድለትም።
5) አንድ ሰው በውስጥም በውጭም ለአላህ መገዛት እና ለመልእክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መታዘዝ አለበት።
ስለዚህ አንድ ሰው የአላህ ቃል እና ትክክለኛውን ሱና በቂያስ (በማመሳሰል)፣ በዘውቅ (በስሜት) እና በካሽፍ (በምስጢራዊ መገለጥ) ፣ በምሁር (ሼክ ወይም ኢማም) አስተያየት ወይም በመሳሰሉት ምንም ነገር መቃወም አይችልም።
6) ትክክለኛ አስተሳሰብ ሁል ጊዜ ከትክክለኛው የራዕይ መገለጥ ጋር ይስማማል። በምክንያታዊ አስተሳሰብ እና በራዕይ መካከል በሁለት ፍጹማዊ ማስረጃዎች ፈጽሞ ሊቃረኑ አይችሉም። በሁለቱ መካከል ግጭት አለ ተብሎ ሲታሰብ አንድ ሰው ራዕይን ከምክንያት ማስቀደም አለበት።
7) በአቂዳ ጉዳይ ዙሪያ በሸሪዓ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላት (ንግግር) መከተል እና ሁሉንም አዳዲስ ቃላት ማስወገድ ያስፈልጋል። ትክክልኛ እና የተሳሳተ ትርጉም ያላቸው አሻሚ ያልሆኑ የሸሪዓ ቃላት ሲኖሩ አንድ ሰው ጥቅም ላይ የዋሉበትን ሁኔታ መመርመር አለበት። ከዚያም እውነትና ትክክል ሆኖ የተገኘው ትርጉም ይረጋገጣል፤ ሐሰት ሆኖ የተገኘው ደግሞ ይከለከላል።
8) ከሃጢያት እና ከስህተት የመጠበቅ ባህሪ ለነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ብቻ የተረጋገጠ ነው። የሙስሊሙ ኡማ በአጠቃላይ በማንኛውም ጥመት ላይ ከመስማማትም ይጠበቃል። ከኡማው ውስጥ ለማንም ግለሰብ ጥበቃ የለም።
ምሁራን እና ሌሎች በተለያዩባቸው ጉዳዮች ማጣቀሻነት የምንጠቀማቸው የአላህ ቃል እና የነብዩ ሱና ናቸው፡፡ ሙስሊሙ ኡማ ውስጥ ኢጅቲሃድ (በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ የሸሪዓን ፍርድ ለመፍረድ ከፍተኛ ጥረት) ለሚያደርጉ ምሁራን ስህተት ቢሰሩ እንኳ ሰበብ ከመስጠት ያስፈልጋል።
9) በሙስሊሙ ኡማ መካከል የሚነገርላቸው እና መገለጥ የሚቀበሉ ግለሰቦች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጻድቅ ህልም መኖሩ እውነታ እና የነቢይነት አካል ነው። በተመሳሳይ መልኩ ጥበብ (ፈራሳህ) መኖር እውነታ ነው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከሸሪዓ ጋር ሲስማሙ ደግሞ የአላህ ተአምራት (ከራማት) እና የምስራች ዜናዎች ናቸው። ይሁንእንጅ የአቂዳ ወይም የሸሪዓ ምንጭ አይደሉም።
10) በሃይማኖት ጉዳይ ላይ በሐሰት መከራከር የሚኮነን ነው። “በተሻለ መንገድ መከራከር” ግን በሸሪዓ የተፈቀደ ነው።
ጠልቆ ወደ ውስጥ መግባቱ በግልጽ የተከለከለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ማክበር እና መከልከል ያስፈልጋል።
አንድ ሙስሊም ሰው የማያውቀውን ነገር ከመናገር መቆጠብም ይኖርበታል። ይልቁንም እንደዚያ ያለውን የእውቀት ጉዳይ ሁሉን ለሚያውቀው አላህ መስጠት አለበት።
11) በሚከራከርበት ጊዜ በራዕይ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለውን ዘዴ መከተል ያስፈልጋል፡፡ በእምነት ጉዳዮች እና እነዚያን እምነቶች እውነት ናቸው ብሎ በሚቀበልበት ጊዜ ያንን ተመሳሳይ ዘዴ መከተል እንደሚያስፈልግ ሁሉ ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው መናፍቅነትን በሌላ መናፍቅነት መቃወም አይችልም፤ ቸልተኝነትን በጽንፈኝነት ወይም በተቃራኒው መጋፈጥም አይችልም።
12) በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ፈጠራ ቢድአ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቢድዓ ጥመት ነው፡፡ ሁሉም ጥመት ደግሞ የእሳት ነው።
ተውሂድ (የአላህ አንድነት) በእምነት እና በእውቀት ውስጥ
1) በአላህ ስሞችና ባህሪያት የማመን መሠረቱ አላህ ለራሱ ያረጋገጠውን ወይም መልእክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለእሱ ያረጋገጡትን ለአላህ ማረጋገጥ ነው፡፡ ስሞቹን እና ባህሪያቱን ከፍጥረቱ ጋር ሳያመሳስል (ተምሲል) ወይም የስሞቹና የባህሪያቱ አፈጻጸም እንዴት እንደሆነ ሳይናገር (ተክይፍ)፤ እንዲሁም አላህ ለራሱ የካደውን ወይም መልእክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለእሱ የካዱትን ከአላህ ማስወገድ ነው፡፡ የስሞቹን እና የባህሪያቱን ቀጥተኛ ትርጉም ሳያዛቡ (ተሕሪፍ) ወይም ሳይክዱ (ተዕጢል) ማለት ነው።
አላህ እንዲህ ብሏል፡-
“እሱን የሚመስል ምንም ነገር የለም፤ እሱም ሁሉን ሰሚ ፣ ሁሉን አዋቂ ነው።”
ይህ ማለት የአላህን ስሞች እና ባህሪያት የሚጠቅሱ እና ትርጉማቸውን የሚያመለክቱ ጽሑፎች ቀጥተኛ ትርጉማቸውን ማመን ማለት ነው።
2) የአላህን ስሞች እና ባህሪያት ከፍጥረቱ ጋር ማመሳሰል (ተምሲል) እና ስሞቹን እና ባህሪያቱን መካድ (ተዕጢል) ክህደት (ኩፍር) ነው።
ልክ እንደ ባጢኒያህ ምሳሌያዊ ትርጓሜ የአላህን ስሞችና ባህሪያት ቀጥተኛ ትርጉም ማዛባት (ተሕሪፍ) – አንዳንድ መናፍቃን ተእዊል ብለው የሚጠሩት የኩፍር ተግባር ነው፡፡ በምሳሌያዊ ትርጓሜዎች የአላህን ባህሪያት የሚክዱ ሰዎች እና ሌሎች ዓይነቶች ደግሞ መናፍቅነትን (ቢድዓ) ያካትታሉ፡፡ ሌሎች ዓይነቶች ደግሞ በስህተት ይከሰታሉ።
3) አላህ በአንድ ሁለንተናዊ ህልውና ውስጥ ነው ብሎ ማመን (ወሕደትል ውጁድ) ፣ አላህ በማንኛውም ፍጥረቱ ውስጥ ነው (ሑሉል) ወይም ከማንኛውም ፍጥረቱ ጋር አንድ ነው (ኢቲሐድ) ብሎ ማመን ሁሉም ከእስልምና የሚያስወጡ የኩፍር እምነቶች ናቸው።
4) የከበሩ መላእክት መኖራቸውን ማመን ያስፈልጋል።
አንድ ሰው ባለው እውቀት መጠን ስለ መላእክት ስሞች ፣ ባህሪያት እና ድርጊቶች ማስረጃው ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ በተለየ ሁኔታ ማመን ያስፈልጋል።
5) አላህ ባወረዳቸው መጽሐፍት ሁሉ ማመን ያስፈልጋል። ቅዱስ ቁርአን ከሁሉም መጽሐፍት በላጭ እንደሆነ እና ከእሱ በፊት የወረዱትን መጽሐፍት በሙሉ እንደሻረ ማመን ያስፈልጋል።
ከቁርአን በፊት የወረዱት መጽሐፍት ላይ የትርጉም መዛባት እንደተከሰተ ማመን ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት ቀደምት መጽሐፍት በመተው ቁርአንን ብቻ መከተል ያስፈልጋል።
6) በሁሉም የአላህን ነቢያት እና መልእክተኞች (ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን) ማመን ያስፈልጋል። ከሰው ልጆች ሁሉ በላጭ እንደሆኑ ማመን ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ የሚል ማንኛውም ሰው ከሐዲ (ካፊር) ነው። ነቢይ ወይም መልእክተኛ መሆኑን የሚያሳይ ትክክለኛ ማስረጃ ካለ በተለየ ሁኔታ ማመን ያስፈልጋል።
የቀሩትን ነቢያት እና መልእክተኞች በተመለከተ መኖራቸውን በአጠቃላይ ማመን ያስፈልጋል። ነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከሁሉም ነቢያት እና መልእክተኞች በላጭ እንደሆኑ ፣ የሁሉም መጨረሻ እና መደምደሚያ እንደሆኑ እና አላህ ለሁሉም የሰው ልጅ እንደላካቸው ማመን ያስፈልጋል።
7) ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በኋላ ራዕይ (ወሕይ) መቋረጡን እና እሳቸው የመጨረሻው ነቢይ እና መልእክተኛ እንደሆኑ ማመን ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ የሚያምን ማንኛውም ሰው ክዷል።
8) የምፅአት ቀን እንደሚከሰት እና ይህን ቀን በተመለከተ በአላህ መጽሐፍ እና በሱና ዘገባዎች የተላለፉትን በሙሉ ማመን የስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ከዚህ በፊት በተከሰቱት ምልክቶች እና ሁኔታዎች ማመን ያስፈልጋል።
9) ውጤቱ መልካምም ይሁን መጥፎ አላህ የወሰነውን ማመን ያስፈልጋል። ይህ ማለት አላህ ከመፍጠሩ በፊት ምን እንደሚሆንና እንደሚከሰት ያውቅ እንደነበር ፣ በለህዋል መህፉዝ ላይ እንደጻፈው ፣ አላህ የሻው እንደሚሆን እና ያልሻው ፈጽሞ እንደማይሆን ፣ በእርሱ ፈቃድ ካልሆነ ምንም ነገር እንደማይከሰት ፣ አላህ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ እንደሆነ እና የሁሉም ነገር ፈጣሪ ፣ የሚፈልገውን አድራጊ እንደሆነ ማመንን ያካትታል።
10) በምሳሌያዊ ትርጓሜ (ተእዊል) ሳይሆን በማስረጃ በተረጋገጡ የሩቅ ዓለም ጉዳዮች እንደ አርሽ ፣ ኩርሲይ ፣ ጀነት ፣ ጀሐነም ፣ በቀብር ውስጥ ያለው ደስታ እና ቅጣት ፣ ሲራጥ ፣ ሚዛን እና ሌሎች የሩቅ ዓለም ጉዳዮች ላይ ማመን ግዴታ ነው።
11) በነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ምልጃ እና በትክክለኛ ማስረጃ እንደተገለፀው ሌሎች ነቢያት ፣ መላእክት ፣ ጻድቃን በትንሳኤ ቀን በሚያደርጉት ምልጃ ማመን ያስፈልጋል።
12) አማኞች በትንሳኤ ቀን ጀነት ውስጥ እና በስብሰባው ምድር ሜዳው ላይ እንደቆሙ ጌታቸውን እንደሚያዩ እውነት ነው። ይህ በመጨረሻው ዓለም መከሰቱን የሚክድ ሁሉ ጠሟል።
በዚህ ዓለም አላህን ማየት አይቻልም።
13) ለአላህ ቅርብ በሆኑ (አውሊያእ) እና በጻድቃን የተፈጸሙ ተአምራት (ከራማት) መኖራቸው እውነታ ነው። ያልተለመደ ክስተት መከሰቱ የግድ ተአምር መከሰቱን አያመለክትም። ይልቁንም ይህ ዓይነቱ ክስተት አንድን ግለሰብ ወደ ጥፋት ለመሳብ በአላህ ማታለል ወይም በሰይጣናት እና በጠንቋዮች ችሎታ ምክንያት ሊከሰት ይችላል። ይህን ለማወቅ መመዘኛው ክስተቱ እና ግለሰቡ ከቁርአን እና ከሱና ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑ መለየት ነው።
14) አማኞች ሁሉ ለአላህ ቅርብ ከሆኑ (አውሊያእ) መካከል ናቸው። እያንዳንዱ አማኝ እንደየ እምነቱ ደረጃ ለአላህ ቅርበት አለው።
ተውሂድ በዓላማ እና በግብ ውስጥ (ተውሂድ አል-ኡሉሂያህ)
1) አሏህ አንድ እና ብቸኛ ነው። በድርጊቶቹ (ሩቡቢያህ) እና በአምልኮው (ኡሉሂያህ) ወይም በስሞቹና በባህሪያቱ (አስማኡ ወሲፋት) ተጋሪ ወይም ባላንጣ የለውም። እሱ የአለማት ጌታ ነው፡፡ የአምልኮ ተግባራት ሁሉ የሚገባው እሱ ብቻ ነው።
2) ማንኛውንም የአምልኮ ተግባራት ከአላህ ውጭ ላለ አካል ማድረግ የሽርክ ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ ዱአ (ልመና) ፣ እርዳታ መጠየቅ ፣ ድጋፍ መጠየቅ ፣ ስለት መሳል ፣ ማረድ ፣ መመካት ፣ መፍራት ፣ ተስፋ ማድረግ ፣ መውደድ እና የመሳሰሉት ድርጊቶች ናቸው፡፡ አምልኮ የሚቀርብለት መላእክት ይሁኑ ፣ የተላኩ ነቢያት ይሁኑ ፣ ጻድቅ የአላህ ባሪያ ወይም ሌላ ማንኛውም ይሁን አምልኮን ከአሏህ ውጭ ላለ ነገር ማድረግ አይፈቀድም።
3) ከኢባዳ (ከአምልኮ) መሰረቶች መካከል አላህን በፍቅር ፣ በፍርሃት እና በተስፋ ማምለክ ነው። ከእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ሌሎቹን ትቶ በአንዱ ብቻ አላህን ማምለክ ጥመት ነው። በእርግጥ አንዳንድ ምሁራን እንዲህ ብለዋል፡- “አላህን በመውደዱ ብቻ የሚያመልክ ሙናፊቅ (ዚንዲቅ) ነው፡፡
የአላህን ቅጣት በመፍራት ብቻ አላህን የሚያመልክ ሐሩሪ [ከጽንፈኛ የኸዋሪጅ ቡድን] ነው፡፡ አላህን ከምህረቱ ተስፋ በማድረግ ብቻ የሚያመልክ ደግሞ ሙርጂኢ [አንድ ሰው እምነት ካለው በኋላ ድርጊቶቹ ሊጎዱት እንደማይችሉ ያመነ መናፍቃዊ ቡድን] ነው።”
4) ፍጹም መታዘዝ ለአላህ እና ለመልእክተኛው ብቻ የሚገባ ነው።
አላህ ብቻ ዳኛ እንደሆነ ፣ እሱ ብቻ ጌታ እንደሆነ እና እሱ ብቻ ሊመለክ እንደሚገባው ማመን በአላህ የማመን አካል ነው። በፍርዱም ሆነ በትእዛዙ ምንም አጋር የለውም። አላህ ያልፈቀደውን ነገር መደንገግ ፣ በሰዎች በፈጠሯቸው እና በፃፏቸው ህጎች መዳኘት እና እንዲህ ባሉ ህጎች ሰዎችን ማስተዳደር ፣ ከሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሸሪዓ ውጭ መከተል ወይም ማንኛውንም የሸሪዓ ክፍል በሰው ሰራሽ ህጎች መተካት ክህደት ነው።
5) አላህ ካወረደው ውጭ መፍረድ ትልቁ ኩፍር (ኩፍር አክበር) ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከእውነተኛ ኩፍር ያነሰ ኩፍር (ኩፍር ዱና ኩፍር) ነው። የፊተኛው ምሳሌ ከአላህ ሸሪዓ ውጭ በሆነ ሸሪዓ መገዛት ወይም መፍረድ መፍቀድ ነው። የኋለኛው ምሳሌ አንድ ሰው ፍላጎቱን ለሟሟላት ሲል ለሸሪአው ታዛዥ ሆኖ ሳለ በተወሰነ ክስተት ከአላህ ሸሪአ መዞር ነው።
6) ሃይማኖትን ምሥጢራዊ እውነታ (ሐቂቃህ) ብሎ በመከፋፈል ለተመረጡት ሙስሊሞች ብቻ የሚመቸውን እና ከሌሎች ሙስሊሞች በተለየ መልኩ የሚከተሉት እንዲሁም ለሌሎች ሙስሊሞች ብቻ የሚመች ውጫዊ ሸሪዓ (ከምርጦቹ በተለየ) ወይም ፖለቲካን ወይም ሌሎች ጉዳዮችን ከሃይማኖት መለየት ሁሉ ሐሰት ነው።
በእርግጥ ከሸሪዓ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ነገር ምሥጢራዊ እውነታም ይሁን፣ ፖለቲካም ይሁን ወይም ሌላ ነገር ከሸሪዓ ጋር ባለው ልዩነት መጠን ወይ ክህደት (ኩፍር) ወይም ደግሞ ጥመት ነው።
7) ከአላህ በስተቀር ሩቅን የሚያውቅ የለም። ከአላህ ውጭ ማንኛውም ሰው ሩቅን ያውቃል ብሎ ማመን ክህደት ነው፡፡ ነገርግን አላህ ለአንዳንድ መልእክተኞቹ ከሩቅ ዓለም ጉዳዮች የተወሰኑትን እንደገለፀላቸው እናምናለን።
8) የአንድ ኮከብ ቆጣሪ ወይም ጠንቋይ ትንበያዎችን እውነት መሆናቸውን ማመን ክህደት (ኩፍር) ነው። ስለወደፊቱ ጊዜ ለመጠየቅ ወደ እርሱ መቅረብ ከባድ ሃጢያት ነው።
9) በቁርአን ወደ አላህ መቃረቢያ መንገድ (አል-ወሲላህ) እንድንፈልግ የታዘዝነው በሸሪዓ በተደነገጉ የተለያዩ የታዛዥነት እና የአምልኮ ተግባራት በመፈፀም ነው። ወደ አላህ መቃረቢያ መንገዶች (አተወሱል) ሶስት ዓይነት ናቸው፡-
ሀ) በሸሪዓ የተደነገገ መንገድ፡ ይህም የአላህን ስሞች በመጥራት እና ባህሪያቱን በመግለጽ ወይም አንድ ሰው የፈጸማቸውን መልካም ተግባራት በመጥቀስ ወይም በሕይወት ያለ መልካም ሰው ለእርሱ ዱአ እንዲያደርግለት በማድረግ አላህን መለመን ነው።
ለ) የመናፍቅነት (የቢድአ) መንገድ፡ ይኸውም በሸሪዓ ውስጥ ያልተጠቀሱ መንገዶችን በመጠቀም ወደ አላህ መቃረብ ነው፡፡ ለምሳሌ አላህን በነቢያትና በጻድቃን ስም ፣ እሱ ዘንድ ባላቸው ደረጃ ፣ በእሱ ላይ ባላቸው መብት ወይም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ አላህን መለመን ነው።
ሐ) የሽርክ መንገድ፡ ይኸውም ሙታንን በአምልኮ ውስጥ በራስ እና በአላህ መካከል አማላጅ አድርጎ በመውሰድ ለእነርሱ በመጸለይ ፣ ፍላጎትን ለማሟላት እነሱን መጥራት ድረሱልኝ ብሎ በመለመን ፣ እርዳታቸውን መጠየቅ እና የመሳሰሉ ድርጊቶችን ይይዛል።
10) በአንድ ነገር ውስጥ በረካ (ብዙ መልካም ነገር መጨመር እና መቀጠል) በአላህ ፈቃድ ይከሰታል። እሱ ከፍጥረታቱ መካከል የሻውን ለሚሻው ይመርጣል። ስለዚህ አንድ ሰው በረካ [በአንድ ነገር ወይም ሰው ላይ] መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከሌለ በስተቀር ማረጋገጥ አይችልም። አንዳንድ ጊዜ ልክእንደ “ለይለቱል ቀድር” ፣ ከቦታዎች (ልክእንደ ሶስቱ መስጊዶች) ፣ ከመጠቃቀሚያዎች ደግሞ (ልክእንደ ዘምዘም ጉድጓድ) ፣ ከድርጊቶች (ልክእንደ መልካም ተግባር) እና ከሰዎች ደግሞ (እንደ ነቢያት) ላይ ይገኛል።
ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በስተቀር በማንኛውም ሰው አካል ወይም ቅሪት አካል ላይ በረካን መፈለግ አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም ከእሳቸው ውጭ በዚህ ኡማ ውስጥ በማንኛውም ግለሰብ ላይ በረካ መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለምና ነው። በእሳቸው አማካኝነት በረካን መፈለግ ከሞቱ በኋላ ቆሟል።
11) በረካን መፈለግ በሸሪአ ከተረጋገጡ ጉዳዮች (ተውቂፍ) መካከል ነው። ስለዚህ ማስረጃው በተጠቀሰበት ነገር ላይ ብቻ በረካን መፈለግ ይፈቀዳል።
12) መቃብር በሚጎበኙ ሰዎች ሶስት ዓይነት ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡-
ሀ) በሸሪአ የተደነገጉ ድርጊቶች፡ ይኸውም የመጨረሻውን አለምን ለማስታወስ ፣ ሙታንን ሰላም ለማለት እና ዱአ ለማድረግ መቃብሮችን መጎብኘት ነው።
ለ) የመናፍቅነት (የቢድአ) ድርጊቶች፡ ይኸውም የተውሂድን ፍጹምነት የሚክድ እና ወደ ሽርክ የሚያመራ ማንኛውም ድርጊት ነው። ለምሳሌ፡- በጻድቃን መቃብር ላይ አላህን ለማምለክ እና ለመቅረብ መፈለግ ፣ የሙታንን በረካ መፈለግ ፣ የመልካም ሥራቸውን ምንዳ ለሙታን እንኩ ማለት ፣ ወደ ጻድቃን መቃብር በመጓዝ መሰል ድርጊቶችን መፈፀም የተከለከለ እና በሸሪዓ ምንም አይነት መሠረት የሌለው ነው።
ሐ) የሽርክን ተግባራትን የያዙ እና የአንድን ሰው ተውሂድ የሚሽሩ ድርጊቶች፡ ይኸውም ማንኛውንም የአምልኮ ተግባር ለሙታን ማድረግ ፣ እርዳታቸውን መጠየቅ ፣ መቃብራቸውን መዞር ፣ ለእነሱ በማረድ እና ለእነሱ ስለት መሳል ወዘተ ናቸው።
13) መንገዶች የዓላማቸውን ህግ ይይዛሉ። ስለዚህ በአላህ አምልኮ ውስጥ ወደ ሽርክ ወይም በሃይማኖት ውስጥ ወደ መናፍቅነት የሚመራ ማንኛውንም መንገድ መከልከል ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሁሉም ፈጠራ (ቢድአ) ጥመት ነው፣ ሁሉም ጥመት ደግሞ የእሳት ነው።
እምነት (ኢማን)
1) እምነት በቃል እና በተግባር ሥራ የተዋቀረ ነው። ተግባራትን በመፈፀም እምነት ይጨምራል፤ ተግባራትን ባለመፈፀም ደግሞ እምነት ይቀንሳል። የልብ እና የምላስ ንግግሮችን ፣ እንዲሁም በልብ ፣ በምላስና በከንፈር የሚፈጸሙ ተግባራትን ያካትታል።
የልብ ንግግር እምነቱ እውነት ነው ብሎ ማረጋገጡ ነው።
የምላስ ንግግር ለእነዚህን እምነቶች እውቅና መስጠት ነው።
የልብ ሥራዎች ለአላህ እጅ መስጠት ፣ አላህን ብቻ ማምለክ ፣ ለእሱ መተናነስ ፣ መልካም ሥራዎችን መውደድና መመኘት ናቸው።
በአካል የሚሰሩ ስራዎች አላህ ያዘዘውን መስራት እና አላህ የከለከለውን መከልከል እና መተው ነው።
2) ሥራዎችን ከእምነት የሚለይ ሙርጂኢ ነው። በእምነት ውስጥ የሌለውን ነገር የሚፈጥር እና የሚጨምር መናፍቅ ነው።
3) ለሁለቱን የእምነት ምስክርነት ቃሎች እውቅና የማይሰጡ (የማይመሰክሩ) ሰዎች የእምነት ማዕረግ አይሰጣቸውም፡፡ እንዲሁም በእነዚያ ግለሰቦች ላይ በዚህ ዓለምም ሆነ በመጨረሻው ዓለም ህጉ አይረጋገጥም።
4) “እስልምና” እና “ኢማን” የሚሉት ሁለትቃላት በሸሪዓ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው። በእነዚህ ሁለት ቃላት መካከል በአንድ መልኩ የጋራ ትርጉም ያላቸው ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የተለየ ትርጉም አላቸው።
አህለል ቂብላህ “በሶላታቸው ወደ ቂብላህ የሚዞሩ” ሙስሊሞች ተብለው ይጠራሉ።
5) ከባድ ኃጢአት (ከቢራህ) የፈጸመ ሰው ከእምነት አይወጣም (ማለትም ከሐዲ አይደለም)። ነገርግን በዚህ ዓለም ያልተሟላ እምነት ያለው አማኝ ተብሎ ይጠራል። በመጨረሻው ዓለም በአላህ ፈቃድ ሥር ነው፤ ከፈለገ ይምረዋል ፣ ከፈለገ ደግሞ ይቀጣዋል።
6) ከአህለል ቂብላህ ውስጥ የተወሰነ ሰው ወደ ጀነት ወይም ወደ ጀሀነም እንደሚገባ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፤ ለዚያ ሰው እንዲህ የሚል የተለየ ጽሑፍ ካልኖረ በስተቀር ማለት ነው።
7) “ኩፍር” የሚለው ቃል በሸሪዓ አጠቃቀም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ከእስልምና የሚያስወጣ ትልቁ “ኩፍር” እና ከእስልምና የማያስወጣ ትንሹ “ኩፍር” ነው። ብዙውን ጊዜ ትንሹ ኩፍር የሥራ ኩፍር (ኩፍር ዐመሊ) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የእምነት ተፃራሪ ነው፡፡
8) አንድን ግለሰብ ከሐዲ (ካፊር) ብሎ መክሰስ ከሸሪዓ ህጎች መካከል ነው። ስለዚህ መሠረታዊ ምክንያቶቹ በአላህ መጽሐፍ እና በሱና ውስጥ ይገኛሉ። ስለዚህ አንድን ሙስሊም በማንኛውም ንግግሩ ወይም ድርጊቱ ከሐዲ (ካፊር) ብሎ መክሰስ አይፈቀድም፤ ድርጊቱ ክህደት መሆኑን የሚያመለክት ከሸሪዓ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ማለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ሸሪዓ ንግግሩ ወይም ድርጊቱ ክህደት መሆኑን ቢወስንም ግለሰቡ ላይ ሁሉም የዚህ ህግ ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ እና ሁሉም እንቅፋቶች (እንደ ድንቁርና እና አለማወቅ) እስካልተወገዱለት ድረስ ካፊር ነው ብሎ ማረጋገጥ አስፈላጊ አይደለም።
አንድን ሙስሊምን ከሐዲ (ተክፊር) ብሎ መክሰስ ከሸሪዓ በጣም አደገኛ ህጎች መካከል ስለሆነ አንድ ሰው ላይ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከማድረግዎ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ እና ማረጋገጫ ማግኘት ያስፈልጋል።
ቁርአን እና የአላህ የንግግር ባህሪ
1) ቁርአን በአረፍተ ነገሩም ሆነ በትርጉሙ የአላህ ቀጥተኛ ንግግር ነው። የወረደ (የተገለጠ) እና ያልተፈጠረ ነው። ከአላህ የመጣ ሲሆን የፍርድ ቀን ከመምጣቱ በፊት ከምድር ተነስቶ ወደ እርሱ ይመለሳል። የነቢዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እውነተኛነት የሚያመለክት የማይደገም ተአምር ነው። ጽሑፉ እና ትርጉሙ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ከማንኛውም መበላሸት የተጠበቀ ነው።
2) አላህ የፈልገውን ፣ በፈለገው ጊዜ እና በፈለገው መንገድ ይናገራል። ንግግሩ በፊደላትና በድምፅ መሆኑ እውነታ ነው። የንግግሩን ሁኔታ አናውቅም፤ ወደዚያም አንገባም።
3) የአላህ ንግግር ከቁርአን ቃላት ውጭ ትርጉሞችን ብቻ ያካትታል የሚሉ መግለጫዎች ፣ ቁርአን የአላህ ንግግር ነጸብራቅ (ሂካያህ ወይም ዒባራህ) ብቻ ነው የሚሉ መግለጫዎች ፣ ቁርአን የአላህ ንግግር በምሳሌያዊ መንገድ ብቻ ነው የሚሉ መግለጫዎች ፣ ቁርአን ከነቃው አእምሮ የሚፈስ (ፈይድ) ነው የሚሉ መግለጫዎች ወይም ከእነዚህ ጋር የሚመሳሰሉ መግለጫዎች ሁሉ ጥመት ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ክህደት ናቸው።
4) ከቁርአን ውስጥ ማንኛውንም ነገር የሚክድ ወይም ጽሑፉ ጠፍቷል ፣ ተጨምሮበታል ወይም ተበላሽቷል ብሎ የሚናገር ከሐዲ ነው።
5) ቁርአንን በሰለፎች ዘዴ (ማለትም በቁርአን እና በሱና ፣ ከዚያም በነቢዩ ባልደረቦች ንግግር ፣ ከዚያም በተከታዮቻቸው ንግግር) መሠረት ማብራራት ያስፈልጋል። ቁርአንን በግል አስተያየት ብቻ ማብራራት አይፈቀድም፡፡
ምክኒያቱም ያለ እውቀት ስለ አላህ መናገር ነውና። ቁርአንን በባጢኒያህ ምሳሌያዊና ምሥጢራዊ ትርጓሜዎች ወይም በተመሳሳይ መንገድ ማብራራት ክህደት ነው።
የአላህ ውሳኔና አስቀድሞ መወሰን (ቀደር)፡
1) ከእምነት ምሰሶዎች መካከል አላህ የወሰነው ውጤቱ መልካምም ይሁን መጥፎ ማመን ነው። ይህ በሚከተሉት ጉዳዮች ማመንን ያካትታል፡-
ቀደርን በሚጠቅሱ ጽሑፎችን ሁሉ ማመን። በአራት የአላህን ውሳኔ ደረጃዎች ማመን፡
- የአላህ እውቀት ዘላለማዊ መሆኑን
- አላህ እስከ እለተ ቂያማ ድረስ የሚሆነውን ሁሉ በለህዋል መህፉዝ ላይ መጻፉን
- በአላህ ሁሉን አቀፍ ፈቃድ እና
- አላህ ሁሉንም ነገር መፍጠሩን
የአላህን ውሳኔ የሚመልስ ወይም ፍርዱን የሚያሻሽል ማንም አለመኖሩን ማመን ግዴታ ነው።
2) በሆነ ነገር ላይ የአላህ ማሰብ እና ማዘዝ በመጽሐፉ እና በሱና እንደተጠቀሰው ሁለት ዓይነት ነው፡-
- የመፍጠር (ቀደሪ ከውኒ) ዓላማ እና ትእዛዝ፡ ይህም ማለት እንዲህ ያለውን ነገር ፈልጎ ፈጥሯል ማለት ነው፡፡
- ሃይማኖታዊ (ሸርኢ) ዓላማ እና ትእዛዝ፡ ይህ አላህ ያሰበውን እና ያዘዘውን መታዘዝ እና መውደድን ያስገድዳል፡፡ ነገር ግን የግድ መፍጠርን አይጠይቅም።
አንድ ፍጡር ሁለቱም ዓላማ እና ፈቃድ ቢኖረውም ዓላማው እና ፈቃዱ ግን ከፈጣሪ ዓላማና ፈቃድ በታች ነው።
3) ባሪያዎችን መምራት እና ማሳሳት በአላህ እጅ ብቻ ነው። አላህ በቸርነቱ የመራቸው አሉ፤ በፍትሃዊነቱ ሊሳሳቱ የሚገባቸውም አሉ።
4) ባሪያዎችም ሆኑ ድርጊቶቻቸው የአላህ ፍጥረታት ናቸው። ስለዚህ አላህ የሰዎች ድርጊት ደራሲ ሲሆን እነርሱም የድርጊታቸው እውነተኛ ፈጻሚዎች ናቸው።
5) የአላህ ድርጊቶች ጥበብን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ። በፈጣሪ ፈቃድ ምክንያት መኖራቸውን ማረጋገጥ።
6) የሁሉም ሰዎች የህይወት ዘመን ተጽፈዋል፡፡ እንዲሁም በህይወት ዘመናቸው የሚኖራቸው የሲሳይ መጠን ተወስኗል። የሰው ልጆች በመጨረሻው ዓለም የሚኖራቸው ደስታ ወይም ሀዘን ከመፈጠራቸው በፊት ተጽፏል።
7) አንድ ሰው የአደጋ እና የህመም መከሰት የአላህ ውሳኔ (ቀደር) ነው ሊል ቢችልም ስህተቶቹን እና ኃጢአቶቹን ግን በአላህ ውሳኔ (ቀደር) ነው ማለት አይፈቀድለትም። ይልቁንም ከስህተቶቹ እና ከኃጢአቶቹ ንስሃ መግባት አለበት፡፡ ያንን ኃጢአት የፈጸመው ሰው በድርጊቱ ሊወቀስ ይገባል።
8) በምክንያት ብቻ መመካት እና መደገፍ በተውሂድ ውስጥ ሽርክ ነው፡፡ በአላህ ላይ ብቻ በመመካት ትክክለኛ እና ተገቢ ድርጊቶችን ከመፈፀም ሙሉ በሙሉ መራቅ ሸሪዓን ማንቋሸሽ ነው፡፡ ሰበብ የማድረስ ተፅዕኖ መካድ ሸሪአን እና ምክኒያታዊነትን ይቃረናል። በአላህ ላይ መመካት (ተወኩል) አስፈላጊ የሆኑትን ትክክለኛ መንገዶች መከተልን አይሽርም።
የሙስሊም ማህበረሰብ (ጀማዓ) እና አመራሩ (ኢማማህ)
1) በዚህ አገላለፅ ውስጥ የማህበረሰብ ትርጉም የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ባልደረቦች እና እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ መንገዳቸውን የያዙ ተከታዮቻቸው ናቸው። እነሱ “ከዳነችው ቡድን” ናቸው። አንዳንድ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ስህተት ቢሠራም መንገዳቸውን የሚከተል ማንኛውም ሰው ከማህበረሰቡ (ከጀማዓው) ነው።
2) በሃይማኖት ውስጥ በቡድን መከፋፈል ወይም በሙስሊሞች መካከል አለመግባባት መፍጠር አይፈቀድም። ሙስሊሞች በሚለያዩባቸው ጉዳዮች የአላህን መጽሐፍ ፣ የመልእክተኛውን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱና እና የሰለፎች መንገድ መመልከት ያስፈልጋል።
3) ከማህበረሰቡ የወጣ ማንኛውም ሰው “በጥሩ መንገድ” ሊጠራ እና ሊመከር ፣ ሊከራከርበት እንዲሁም ማስረጃው በእሱ ላይ ሊቆም ይገባል። ንስሃ ከገባ መልካም ነው፤ አለበለዚያ በሸሪዓው የሚገባውን ይቀጣል ያገኛል።
4) በአላህን መጽሐፍ ፣ በሱና እና በሰለፎች ስምምነት የተረጋገጡ ትርጉሞችን በሙስሊሞች ላይ መጫን ያስፈልጋል። ሙስሊሞችን በአጠቃላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ባሉ ረቂቅ ጉዳዮች እና ጥልቅ ትርጉሞች መፈተን አይፈቀድም።
5) ሁሉንም ሙስሊሞች የሚመለከቱ አጠቃላይ ህጎች ተቃራኒው እስኪገለጥ ድረስ መልካም አላማ እና ትክክለኛ እምነት አላቸው። አጠቃላይ ህጉ ቃሎቻቸውን በተሻለ መንገድ መተርጎም ነው። ሆኖም እውነትን እና መጥፎ ዓላማን የሚቃወም ሰው የቃሎቹን እና የድርጊቶቹን ትክክለኛ ማብራሪያ ለመስጠት ከመጠን በላይ መጣር አይፈቀድም።
6) ከሱና ውጭ ያሉ የሙስሊም ቡድኖች (አህለል ቂብላህ) በዚህ ዓለም ጥፋት እና በመጨረሻው ዓለም ቅጣት ያስተናግዳሉ።
በውስጡ ክህደት ከያዘ ሰው በስተቀር በእነሱ መካከል ያለው ማንኛውም ህግ በአላህ ቅጣት ስጋት ሥር ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሆኖም ከእስልምና ውጭ ያሉ የሐሰት ሙስሊም ቡድን ተከታዮች በአጠቃላይ ከሐዲዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። ከእነሱ መካከል ያለ ማንኛውም ግለሰብ ከሃዲዎች ጋር ተመሳሳይ ነው።
7) የጁምአ እና የጀማዓ ሶላቶች ከእስልምና ታላላቅ ውጫዊ ምልክቶች መካከል ናቸው። እውነተኛ ማንነቱ የተደበቀ ሙስሊምን ተከትሎ መስገድ ሶላቱ ትክክል እና ተቀባይነት ያለው ነው። የአንድን ሰው እውነተኛ ማንነት ሳያውቁ ተከትየ አልሰግድም ማለት ደግሞ መናፍቅነት ነው።
8) አንድ ሰው ሌላውን ተከትሎ መስገድ ቢችልም በግልጽ መናፍቅነትን ወይም አመጸኝነትን የሚያሳይን ሰው ተከትሎ መስገድ አይፈቀድም። እንዲህ ዓይነቱን ሰው ተከትሎ ሶላት መስገድ ሶላቱ ትክክል ነው፡፡
ያንን ሶላት የሰገደው ሰው ግን ኃጢያት ሠርቷል፣ ከእንዲህ ዓይነት ሰው ጀርባ በመስገድ ትልቅ ክፋትን ለመከላከል እስካልሆ ድረስ ማለት ነው። ሆኖም አንድ ሰው ከእሱ ጋር የሚመሳሰል እና ተከትሎት ሊሰግድ የሚችል ሰው ማግኘት ካልቻለ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዲህ ዓይነት ሰዎች ተከትሎ መስገድ ይፈቀዳል።
በማንኛውም ሁኔታ የጀማአን እና የጁምአን ሶላት መተው አይፈቀድም። ከሐዲ ነው ተብሎ ከተፈረጀ ሰው ጀርባ በማንኛውም ሁኔታ መስገድ አይፈቀድም።
9) የሙስሊሞች አመራር (አል-ኢማማህ) የሚወሰነው በሙስሊሙ ኡማ ስምምነት ወይም ገዥን የመሾምና የማንሳት መብት ባላቸው የሙስሊሙ ኡማ አባላት (አህለል ሐል ወል-አቅድ) በሰጡት የድጋፍ ቃል ነው።
በተመሳሳይ መልኩ አላህን መታዘዝ ያዘን መታዘዝ ፣ ኃይል በመጠቀም ሥልጣንን ለያዘ ምክር መስጠት እና የሙስሊሙን ኡማ ከጀርባው ማሰባሰብ ያስፈልጋል። ማስረጃ ያለው ግልጽ ክህደት (ኩፍር) እስካላሳየ ድረስ ገዥውን በማንኛውም ሁኔታ ማመፅ የተከለከለ ነው።
10) ሙስሊም መሪዎች ምንም ያህል ጨቋኞች ቢሆኑ ከእነሱ ጋር ሶላት መስገድ ፣ ሐጅ እና ጅሃድ ማድረግ ያስፈልጋል።
11) ሙስሊሞች አለማዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያቶች ወይም በጃሂሊያህ የጎሳ ኩራት ምክንያት እርስ በእርስ መዋጋታቸው የተከለከለ ነው። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ከትላልቅ ኃጢያቶች መካከል ናቸው።
ሆኖም መናፍቃንን ፣ በገዣቸው ላይ ያመፁትን እና እነዚህን በትናንሽ እርምጃዎች ማቆም ካልተቻለ እነሱን መዋጋት ይፈቀዳል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ እነዚህን ቡድኖች መዋጋት ግዴታ ይሆናል። ይህ የሚወሰነው በሚያስገኙት ጥቅም እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በበማስገባት ነው።
12) የነቢዩ ባልደረቦች ሁሉ ታማኞች (`አዱል) ናቸው። እነሱ የዚህ ሙስሊም ኡማ ምርጦች ናቸው። በእምነታቸው እና በሙስሊሙ ኡማ ዘንድ ያላቸውን ክብር መመስከር ከሃይማኖት ግዴታ ያደረገው ፍጹም መሠረታዊ ነጥብ ነው። እነሱን መውደድ ሃይማኖት እና እምነት ሲሆን እነሱን መጥላት ደግሞ ክህደት እና መናፍቅነት ነው። በእነሱ መካከል በተፈጠሩ አለመግባባቶች ውስጥ ከመግባት መቆጠብ እና ክብራቸውን ከሚቀንስ ርዕስ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ ያስፈልጋል።
ከእነሱ መካከል በላጮቹ አቡበክር ፣ ከዚያም ኡመር ፣ ከዚያም ዑስማን ፣ ከዚያም አሊ ናቸው። እነሱ በትክክል የተመሩ የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ተተኪዎች ናቸው። ለእያንዳንዳቸው የተተኪነት መብት የሚሰጣቸው እንደ ታሪካዊ ቅደም ተከተላቸው ነበር።
13) የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቤተሰቦች መውደድ እና መደገፍ ፣ የእሳቸውን ሚስቶች (የአማኞች እናቶች) ደረጃ ከፍ ማድረግ እና ክብራቸውን ማወቅ ፣ ሰለፎችን መሪዎች መውደድ ፣ የሱና ምሁራንን እና እነሱን የሚከተሉትን መውደድ እንዲሁም ከመናፍቃን እና ከፍላጎታቸው መራቅ ከሃይማኖት ነው።
14) በአላህ መንገድ ላይ ጅሃድ ማድረግ የእስልምና ከፍተኛው ደረጃ ነው። ሰዓቷ እስከትቆም ድረስ ህጋዊ ሆኖ ይቀጥላል።
15) በመልካም ነገር ማዘዝ (አል-መዕሩፍ) እና ከክፉ ነገረ መከልከል (አል-ሙንከር) ከታላላቅ የእስልምና ውጫዊ ምልክቶች መካከል ነው። የሙስሊሙን ማህበረሰብ ከሚጠብቁ ሰበቦች መካከል ነው። እንዲህ ያለው ተግባር የሚያስገኘውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት አንድ ሰው በቻለው አቅም መስራት ይኖርበታል።
የአህለ ሱና ወልጀማዓ ባህሪያት እና ልዩ መለያዎች
አህለ ሱና ወልጀማዓ በመጨረሻው ዓለም “የምትድነው ቡድን” ሲሆኑ በዚህ ዓለም ደግሞ “አሸናፊዋ ቡድን” ናቸው።
በእነሱ መካከል ልዩነት ቢኖርም ከሌሎች ሁሉ የሚለዩዋቸው የተወሰኑ ባህሪያት እና መለያዎች አሏቸው። እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡-
1) የአላህን መጽሐፍ በመሀፈዝ (በመሸምደድ) ፣ በመቅራት እና በመተርጎም እንዲሁም የነቢዩን ሐዲሶች በማወቅ ፣ ትርጉማቸውን በመረዳት እና ትክክለኛውን ከደካማው በመለየት ለአላህ ቃል ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ምክንያቱም የአላህ ቃልም ሆነ የነቢዩ ሐዲስ የእምነትን እና የህግ እውቀት ምንጭ ናቸውና። በተጨማሪም እውቀታቸውን በተግባር ያስከተላሉ።
2) ወደ ሃይማኖቱ ሙሉ በሙሉ ይገባሉ። በሁሉም መጽሐፍት ያምናሉ። እንዲሁም የአላህን የሽልማት ቃል እና የቅጣት ማስጠንቀቂያውን በሚጠቅሱ ጽሑፎችን ያምናሉ። የአላህን ባህሪያት የሚያረጋግጡ እና ከፍጥረቱ ጋር መመሳሰሉን የሚክዱ ጽሑፎች ያምናሉ።
በአላህ ውሳኔ (ቀደር) መኖር ፣ የአላህ ባሪያ ፍላጎት ፣ ፈቃድ እና ተግባር ያለው መሆኑን በማረጋገጥ ያጣምራሉ። እንዲሁም በእውቀትን እና በተግባር ፣ በጥንካሬ እና በርህራሄ ባህሪያት ፣ አስፈላጊ እርምጃዎችን በመውሰድ እና ዓለምን በመተው (ዙህድ) ላይ ያጣምራሉ፤ ይሰባሰባሉ።
3) ሱናን ይከተላሉ፤ መናፍቅነት ሁሉ ይቃወማሉ። በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ቡድንተኝነት እና ቲፎዞ ፈላጊነትን ይንቃሉ።
4) በእምነት ፣ በስራ እና ሌሎችን ወደ አላህ በመጣራት ዙሪያ የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ባልደረቦች እና የእነሱን መንገድ የሚተከተሉ የታመኑ ምሁራንን መመሪያ ይከተላሉ። ከነቢዩ ባልደረቦች መንገድ የወጡ ሰዎችን ይርቃሉ።
5) መካከለኛ አቋም ይይዛሉ። ስለዚህ በእምነት ጉዳይ በሁለት ጫፎች መካከል ባሉ ቡድኖች መካከለኛውን አቋም ይይዛሉ። በአምልኮ ተግባራት እና በአኗኗራቸው ደግሞ በጽንፈኞች እና በቸልተኞች መካከል መካከለኛውን አቋም ይይዛሉ።
6) የሙስሊሞች ቃል በእውነት ላይ ለማሰባሰብ ፣ በተውሂድ እና ነቢዩ በመታዘዝ (አል-ኢትቲባዕ) ላይ አንድ ለማድረግ እንዲሁም በመካከላቸው ክርክር እና ልዩነት የሚፈጥሩ ምክንያቶች በሙሉ ለማስወገድ ይጥራሉ።
ከዚህ በመነሳት በሃይማኖቱ መሠረታዊ ነገሮች እራሳቸውን ከሌላው የሙስሊም ኡማ ”አህለ ሱና ወልጀማአ” ከሚለው ስም ውጭ በሌላ ስም አይለዩም። እንዲሁም ከእስልምና እና ከሱና ትስስር ውጭ በሌላ ማንኛውም ትስስር ምክንያት ማንንም አይወዳጁም ወይም አይጠሉም።
7) ሌሎችን ወደ አላህ ይጠራሉ ፣ በመልካም ነገር ያዛሉ ከክፉ ነገር ይከለክላሉ ፣ ጅሃድ ያደርጋሉ ፣ ሱና እንዲያንሰራራ (እንደገና እንዲያብብ) ፣ የአላህን ሸሪአ እና ህግ በትናንሽም ይሁን በትልልቅ ጉዳዮች ላይ ያስፈፅማሉ።
8) ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ፍትሃዊነት እና እኩልነት አላቸው። ስለሆነም ከሰዎች ጋር በሚገናኙበት ጊዜ የራሳቸውን ፍላጎት ወይም የቡድናቸውን ፍላጎት ሳይሆን የአላህን መብት ይጠብቃሉ። በዚህም ምክንያት ሌሎችን አይበዘብዙም ወይም አይበድሉም ፣ እንዲሁም ምንም ቢሆኑ ክብር የሚገባቸውን አያቃልሉም።
9) የሐገራቸው እና የዘመናቸው ርቀት ቢኖርም በመረዳት አንድነት እና በአቋም ተመሳሳይነት አላቸው። ይህ ለሃይማኖታቸው አንድ ምንጭ እና እውቀቱን የሚያገኙበት አንድ ዘዴ በመያዛቸው የተገኘ ውጤት ነው።
10) ለሁሉም ሰው ደግነት ፣ ምህረት እና መልካም ሥነ ምግባር ያሳያሉ።
11) ለአላህ ፣ ለመጽሐፉ ፣ ለመልእክተኛው ፣ ለመሪዎች እና በአጠቃላይ ለሙስሊሞች ቅንነት (ነሲሐ) ያሳያሉ።
12) የሙስሊሞችን ጉዳይ ይጨነቃሉ፣ ያግዛሉ፣ መብታቸውን ይጠብቃሉ እንዲሁም ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይከላከላሉ።
በዶክተር ናስር አል-‘አቅል
ተርጓሚ: አሊ አተሚሚ
የአማርኛ ትርጉም፡ በአህመድ የሱፍ


Share