
ቢድአ የሱና ተቃራኒ ወይም ተፃራሪ ነው። ቢድአ ከተረጋገጡ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የአምልኮት ተግባራት ጋር የሚፃረሩ በአሏህ ሃይማኖት ውስጥ የፈጠራ ተግባራትን ማስተዋወቅ ነው።
ቢድአ ከቁርአን ፣ ከሐዲስ ፣ ከሸሪአ መሰረት የሌለውና በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እና በነዛ ብርቅየ ሶሃቦች ዘመን ያልነበረ ወይም ያልሰሩት እና እንዲሰሩት ያላዘዙት ማንኛውም አይነት የአምልኮት ተግባራት የሚያጠቃልል ሲሆን ሰዎች ከራሳቸው ፍልስፍናና ስሜት በመነሳት ያልነበሩ ነገሮችን በዲነል ኢስላም ላይ መጨመር ወይም መቀነስ ነው።
ምክኒያቱም ይህ በእስልምና ሃይማኖት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በቀር ማንኛውም የአምልኮት ተግባር በአሏህ ተቀባይነት አይኖራቸውም።
- ተግባሩ ከልብ ለአሏህ ብቻ ተብሎ መሰራት አለበት። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሉት ማለት ነው።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪና ሙስሊም)
“የስራዎች ሁሉ ምንዳ መሰረቱ ኒያ (ማሰብ) ነው። እናም ሁሉም ሰው ባሰበው ነገር ላይ ምንዳውን ያገኛል።”
- ተግባሩ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በሰሩበት መንገድ መሰራት አለበት። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ቡኻሪና ሙስሊም)
“በእኛ ጉዳይ (በኢስላም) ላይ የሆነን ነገር የፈጠረ ሰው ያ ከእኛ አይደለም ተመላሽ (ውድቅ) ነው።”
የቢድአ ፍች በእስልምና
- ኢማሙ ሻፊእይ (ረሂመሁሏህ) ከቁርአን ፣ ከሐዲስ ወይም ከሱሐቦቻቸው ንግግር መሰረት የሌለው ማንኛውም የኢባዳ ተግባር ቢድአ ነው ብለዋል።
- ኢብን አልጀውዚ (ረሂመሁሏህ) ቢድአ ማለት በነብዩ (ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም) እና በሶሃቦቻቸው ዘመን ያልነበረ ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ ማንኛውም የኢባዳ አይነት ቢድአ ነው ብለዋል።
- ኢብኑ ረጀብ (ረሂመሁሏህ) ከሸሪአ መሠረት የሌለው ማንኛውም የኢባዳ አይነት ቢድአ ነው ብለዋል።
የቢድአን ፍች ለማጠቃለል ያህል ቢድአ ማለት ከቁርአን ፣ ከሐዲስ ፣ ከሸሪአ መሰረት የሌለው እና በረሱል (ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም) እና በነዛ ብርቅየ ሶሃቦች ዘመን ያልነበረ ወይም ያላደረጉት የኢባዳ ተብየ አይነቶችን ሁሉ የሚያጠቃልል እና ከራሳችን ፍልስፍናና ስሜት በመነሳት ያልነበሩ ነገሮችን በዲነል ኢስላም ላይ መጨመር ነው።
ሁሉም ቢድአ ክልክል እና ውድቅ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ምክኒያቱም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
(ትርሚዚ)
“(በሃይማኖቱ ውስጥ) አዲስ የተፈጠሩ ነገሮችን ተጠንቁ። ሁሉም ፈጠራ ቢድአ ነው። ሁሉም ፈጠራ ጥመት ነው። ሁሉም ጥመት ደግሞ የእሳት ነው” ብለዋል።
የቢድአ አይነቶች

ብዙ የቢድአ አይነቶች አሉ። አንዳንዶቹ የኩፍር ተግባራቶች ናቸው። ለምሳሌ የደጋግ ሙት ሰዎችን እርዳታ መፈለግ እና ለእነሱ እንስሳ ማረድ ይገኙበታል።
አንዳንዶቹ የቢድአ አይነቶች የሽርክ ሃጢያት የሚፈፀሙበት ነው።
ለምሳሌ በመቃብሮች ላይ መገንባት ፣ መስገድ እና ወደ እነሱ መለመን ናቸው። አንዳንዶቹ ያለመታዘዝ ተግባራቶች ናቸው። ለምሳሌ ከጋብቻ መታቀብ እና ያለማቋረጥ መፆም ናቸው።
ሙስሊሞች ሁሉንም የቢድአ አይነቶች ማስወገድና ከእነሱ መራቅ ይኖርባቸዋል። ምክኒያቱም የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሱና ይገልፃሉ፤ የአሏህን ቁጣና ቅጣት ያስከትላሉና ነው።
ቢድአን ለመረዳት የሚያገለግሉ አጠቃላይ ህጎች
- የተፈበረከን (በፈጠራ የተገኘን) ሐዲስ መሠረት በማድረግ የሚደረግ የኢባዳ አይነት ቢድአ ነው። ለምሳሌ በረጀብ ወር የሚደረግ ስግደት
- ረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም ያልሰሩት ያላከናወኑት ማንኛውም ኢባዳ ተብየ ተግባር ቢድአ ነው። ልክ ኒያን ሶላት ከመጀመራችን በፊት እንደ ማሰማትና ከአምስቱ ዋጅብ ሶላቶች ውጭ ላሉ ሱና ሶላቶች አዛን እንደ ማድረግ ማለት ነው።
- እስልምና እንደ ኢባዳ የማይቀበላቸውን ድርጊቶች አሏህን ለማስደሰት በሚል ሰበብ ወይም ኒያ የሚደረጉ ማንኛቸውም የልማድ ድርጊቶች ቢድ አናቸው። ለምሳሌ ያህል ቀጣይነት ያለው ዝምታ ፣ አለመብላት አመጠጣት ፣ አለማግባት ወ.ዘ.ተ
አሏህን ለማስደሰት በሚል ሰበብ የተከለከሉ ነገሮችን መስራት ቢድአ ነው። ባጠቃላይ ሁሉም የኢባዳ ተግባራት ሊሰሩ የሚገባቸው ረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም በሰሩባቸው መንገዶች ብቻና ብቻ ነው። ይህም የሚከተሉትን ስድስት ሁኔታዎች ያሟላ መሆን ይኖርበታል
- የኢባዳ ስራው ከሸሪአ ድንጋጌዎችጋ ሊስማማ ይገባል።
ያለበለዚያ ስራችን ውድቅና በራሳችን ጊዜ የምንጠምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ስለዚህ መወሊድን ማክበር በራሱ ቢድአ ፣ ጥመት ነው። ምክኒያቱም በሸሪአ አልተደነገገም ፣ ሶሃቦች እንዲያከብሩ አልታዘዙምና።
- የኢባዳ ድርጊቱ ከሸሪአ ክፍሎች (ዝርዝር ነገሮች) ጋር ሊስማማ ይገባል።
ስለዚህ አንድ ሰው ከሐጅ ቡኋላ በግመል ወይም በፍየል ፈንታ እንደ መሦዋዕት አድርጐ ፈረስ ቢያርድ ተቀባይነት አይኖረውም።
- ኢባዳው በሸሪአ ከተደነገጉ ነገሮች ጋር በመጠን ሊስማማ ይገባል።
አንድ ሰው በዙሁር ሶላት አራት ረከአ በመስገድ ፈንታ ሁለት ረከአ ጨምሮ ባጠቃላይ ስድስት ረከአ ቢሰግድ ተቀባይነት አይኖረውም። ድርጊቱም ጠማማ ተግባር ነው።
- የኢባዳ ተግባሩ በምን አይነት መንገድ እንደሚከወን ከሸሪአ ጋር ሊስማማ ይገባል።
ስለዚህ አንድ ሰው ውዱእ ሲያደርግ እጁን በመታጠብ ፈንታ እግሩን በማጠብ ቢጀምር ተቀባይነት አይኖረውም።
- ኢባዳው የሚደረግበት ሰዓት ከሸሪአ ጋር ሊስማማ ይገባል።
ፀሀይ ስትጠልቅ የዙሁር ሶላትን መስገድ ተቀባይነት አይኖረውም።
- ኢባዳው የሚደረግበት ቦታ ከሸሪአ ድንጋጌ ጋር ሊስማማ ይገባል።
ማጠቃለያ
አንድን ኢባዳ በረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም መንገድ ለመስራት ኢባዳው በዝርዝር ነገሮች ፣ በመጠን ፣ በቦታ ፣ በሰአትና በምን አይነት መንገድ መከወን እንዳለበት ከሸሪአ ድንጋጌዎች ጋር ሊስማማ ይገባል።
የቢድአ አደጋዎችና የሚያስከትላቸው ውጤቶች
- ቢድአ ለጥመትና ለክፍርና ቀዳሚ የሚያደርግ ወይም ጥመትን የሚያበስር ነው።
- በአሏህ ስም መሠረት የለሽ ንግግር ማድረግን
- ረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለምን ማስተካከል ወይም እንከን አሉባቸው ብሎ ማመን
- ሱና የሆኑ ነገሮችን መተውን
- በሙስሊሞች መሃል ግጭት ማቀጣጠልን
- ረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም የእስልምና መልእክት ሙሉ በሙሉ አላደረሱም ብሎ መውቀስ (መተቸት) ያስከትላል።
ቢድአ ለመስራት ምክኒያቶች
- ድንቁርና
- የራስን ስሜት መከተል
- ጥርጣሬን አጥብቆ መያዝ
- አሊሞች የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተጫወቱ አለመሆ ናቸው።
- በደካማ ወይም በተፈበረኩ ሐዲሶች ላይ ጥገኛ መሆን
- ለሌሎች ሰዎች ስህትተ ድንበር ያለፈ ስሜታዊ ምላሽ መስጠት
- የረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም ሶሐቦች ኢስላማዊ መልእክቶችን ወይም ፅሁፎችን በተረዱባቸው መንገዶች መረዳት አለመቻል
- በጭፍን ከቢድአ ሰዎች ጋር መመሳሰል
የቢድአ ማጥፊያ መንገዶች
- ከቢድአ አደጋዎችና ውጤቶቹ ማስጠንቀቅ
- ሰዎች ቁርአን እና ሱናን ሰለፎቹ በተረዱበት መንገድ እንዲረዱና አጥብቀው እንዲይዙ ጥሪ ማድረግ
- ደካማ (ዶኢፍ) እና ትክክለኛ (ሰሂህ) የሆኑ ሐዲሶችን ለይቶ ማወቅ
- የዲን ትምህርት ቤቶችን ከቢድአ ነገሮች ማፅዳት
- እውቀትን ማስፋፋት
- ሰዎች በእምነታቸው ፣ በአቂዳቸው ላይ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ማስተካከል
- የቢድአ ሰዎችን ማስጠንቀቅ እና ማሸነፍ
- እውቀትን ከትክክለኛ ምንጭ መፈለግ

