​የኢባዳ መሰረቶች

Author picture

​የኢባዳ መሰረቶች ከመዳሰሳችን በፊት ኢባዳ የሚለው ቃል ትርጉም እንመልከት፡፡ ኢባዳ ማለት ሸሪአዊ ፍቹ አሏህ የሚወደው ማንኛውም በግልፅም ይሁን በድብቅ የሚሰራን፤ በንግግር እና በተግባር የሚገልፅን ስራ ሁሉ የሚያጠቃል ቃል ነው።

ሸኹል ኢስላም ኢብንተይሚያ ኢባዳ ማለት አሏህ በመልዕክተኛው ምላስ ያዘዘውን ነገር በመከተል አሏህን መታዘዝ ነው ብለዋል።

ኢብነል ቀይም ከኢባዳ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች ሲገልፁ ኢባዳ በአስራ አምስት መርሆዎች ዙርያ ያጠነጥናል። እነሱንም ያሟላ ኡቡድያን (ለአሏህ ያለውን ባርነት) አሟልቷል።

ኢባዳ በልብ ፣ በምላስ እና በአካል (በመገጣጠሚያዎች) የሚፈፀም ተብሎ የሚከፈል ሲሆን እያንዳዳቸውም ሁሉንም ስራ የሚያጠቃልሉ የሆኑ አምስት አምስት ውሳኔዎች (ህግጋቶች) አሏቸው።

እነዚህም ዋጅብ (ግዴታ) ፣ ሙስታሃብ (የተወደደ) ፣ ሐራም (የተከለከለ) ፣ መክሩህ (የተጠላ) እና ሙባህ (የተፈቀደ) ናቸው ብለዋል። ኢማም ቁርጡብይ የኢባዳ መሰረቱ መተናነስ እና እጅ መስጠት (መታዘዝ) ነው ብለዋል።

ታላቁ ሙፈሲር እና የአልቢዳያ ወኒሃያ አዘጋጅ ኢብን ከሲር የኢባዳን ትርጉም ሲያስቀምጡ ኢባዳ ማለት አሏህ ያዘዘውን ነገር በመስራት የከለከለውን ነገር በመከልከል ለእሱ ታዛዥ መሆን ነው።

የኢስላም ትርጉም ኢስቲስላም ሲሆን ኢስቲስላም ማለት በሙሉ ታዛዥነት እና መተናነስ ለአሏህ እጅ መስጠት ማለት ነው ብለዋል።

ይህን ንግግራቸውንም ሲገልፁ በእርግጥም አሏህ ፍጡራኖችን የፈጠረው እሱን በብቸኝነት እንዲገዙት እና በእሱም ላይ ምንምም ነገር ላያሻርኩ ነው።

አሏህ እሱን ለታዘዘ ሰው የሚመናዳው ሲሆን እሱን ያልታዘዘው ግን ከባድ በሆነ ቅጣት ይቀጣዋል። እሱ ከነሱ የማይፈልግ ሲሆን እነሱ ግን ከእሱ በእያንዳንዱ አጋጣሚና ሁኔታ ይፈልጉታል። ምክኒያቱም የፈጠራቸው ፣ የሚሰጣቸው ፣ የሚነሳቸው እሱ ነውና ብለዋል።

የመፈጠራችን ሚስጥር

እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርነው ለአንድ ታላቅ ለሆነ አላማ ሲሆን ሌሎች የምናቅዳቸውና የምንስራቸው ስራዎች ይህንን ታላቅ አላማ ከዳር ለማድረስ የሚረዱን ናቸው።

ሆኖም አንዳንድ እምነት አልባዎች ፈጣሪ እሚባልም ሆነ ጀነት እና ጀሃነም የሚባል ነገር የለም በማለት የሰው ልጅ የተፈጥሮ ግኝት ወይም የዝግመተ ለውጥ ውጤት እንደሆነ በማሰብ የሰውን ልጅ ያለ አላማ ማስቀረት ይሻሉ።

ነገርግን አሏሁ አዘወጀል እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርንበትን ታላቅ አላማ ቁርአን ላይ በማያሻማ መልኩ ገልፆልናል።

አሏሁ አዘወጀል በሱረቱል ማኢዳ አንቀፅ 56 ላይ እንዲህ ይለናል፦ “በእርግጥ የሰው ልጆችንም ሆነ አጋንትን አልፈጠርኳቸውም እኔን ሊገዙኝ ቢሆን እንጅ።”

“በል! እነሆ ሶላቴ ፣ እርዴ ፣ ህይወቴ ፣ ሞቴ ለአሏህ፤ ለአለማቱ ጌታ ነው። አጋር የለውም።”

{አልቁርአን 6:162}

“እነሆ በአሏህ ላይ ያሻረከ(ያጋራ) በእርግጥ አሏህ ጀነትን በእሱ ላይ እርም አደረጋት። እናም መኖሪያው እሳ ነው። በዳዮችም ረዳቶች የላቸውም።”

{አል-ቁርአን 5:72}

ከኢባዳ ጋር የተያያዙ ጠቃሚ መርሆዎች

1 እውቀት ከስራ ይቀድማል

የሰው ልጅ ማንኛውንም ነገር የሚሰራው መስራት ባሰበው ነገር ላይ እውቀት ሲኖረው ነው። ካልሆነግን ውጤቱ ድካምና ጥፋት ነው።

አንድ ሰው የአንድሮይድ አፕልኬሽን ደቨሎፕ ማድረግ ይፈልጋን እንበል። ሆኖም ግን እንዴት ኮዲንግ ማድረግ እንደሚቻል የማያውቅ ከሆነ ይህ ሰው አፕልኬሽኑን ደቨሎፕ ማድረግ ይችላል? አይችልም! ለምን? እንዴት ኮዲን ማድረግ እንዳለበት እውቀት የለውምና።

በተመሳሳይመልኩ አንድ ሰው ኢባዳ የአምልኮ ተግባራት ለመስራት በሚሰራው ነገር ላይ እውቀት ሊኖረው ይገባል። ያለበለዚያ ስራው ድካም ብቻ ነው የሚሆነው።

አንዳንዴም ወደ ጥፋት ሊመራው ይችላል። ምክኒያቱም ያለ እውቀቱ የቢድአና የሽርክ ተግባራትን ሊሰራ ይችላልና። ኢማሙ ቡኻሪ በኪታባቸው መግቢያ ላይ እውቀት ከስራና ከንግግር ይቀድማል ብለዋል።

ኢብን ሐጀር ለንግግርና ለስራ መስተካከል ቅድመሁኔታው እውቀት ነው። ልክ ለስራ መስተካከል የኒያ መስተካከል ቅድመሁኔታ እንደሆነው ሁሉ ብለዋል።

ትረካ የሚመጣው ከጥናት ቡኋላ እንደሆነው ሁሉ ስራም የሚመጣው ከእውቀት ብኋላ ነው።

2 ለአሏህ ቅን መሆን ወይም ስራን በኢህላስ መስራት

ኢህላስ ማለት ማንኛውንም መልካም ስራ አጥርቶ የአሏህ ምንዳና ውዴታ እንደሚገኝበት አስቦ ለአሏህ ብቻ አድርጎ መስራት ነው።

ይህም ከሰዎች ክብርና ዝና ፣ ስልጣን ፣ ገንዘብ ፣ ለዩዩልኝና ለይስሙልኝ ለሚሉ ነገሮች ተፃራሪ የሆነ ነው። መልካም ስራም ተቀባይነት የሚኖረው ኢህላስ ሲኖረው ነው።

ኢብን መስኡድ ንግግር ያለተግባር አይጠቅምም፤ ተግባርም ያለ ንግግር አይጠቅምም። ሁላቸውም አይጠቅሙም በተስተካከል ኒያ ካልሆነ በቀር፤ ኒያም አይጠቅምም ከሱና ጋር እስካልገጠመ ድረስ ብለዋል።

3 ከሱና ጋር መግጠም

በእርግጥ ይች ቀጥተኛ መንገዴ ናት፤ ተከተሏት።

{አል-ቁርአን 6:152}

አንድ የአምልኮት ተግባር ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው የአምልኮት ተግባሩ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በሰሩበት መንገድ የተሰራ እንደሆነ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ወደ ቢድአ የሚያዘነብልበት ነገር ያመዝናል። የሙዕሚኖች እናት አኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈችው

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በጉዳያችን ያልሆነን (በሃይማኖታችን የሌለን) ነገር የሰራ ሰው እርሱ ተመላሽ ነው (ከእሱ ተቀባይነት የለውም) ብለዋል።

በሌላ ዘገባ የአሏህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ሁሉም ፈጠራ ጥመት ነው፤ ሁሉም ጥመት የሳት ነው ብለዋል።

አሏሁ አዘወጀል የእሱ ውዴታ የሚገኘው መልዕክተኛውን በመከተል ላይ እንደሆነ ሲገልፅ እንዲህ አለ፦

አሏህን የምትወዱ እንደሆናችሁ ተከተሉኝ አሏህ ይወዳችኋል፤ ሃጢያቶቻችሁንም ይምርላችኋል። በእርግጥ አሏህ መሃሪ አዛኝ ነው በላቸው!

{አል-ቁርአን 3:31}

አቡ ኹረይራ (ረ.ዐ) ባስተላለፈው ሐዲስ የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሁሉም ኡመቶቼ ጀነት ይገባሉ እምቢ ያለው ሲቀር አሏቸው። እሱ ማነው እምቢ ያለው? ብለው ሲጠይቋቸው። እኔን የታዘዘ ጀነት ገባ፤ እኔን ያልታዘዘ በእርግጥ እንቢ አለ ብለዋል።

Share

More Posts

Send Us A Message

Scroll to Top