ኢብሊሰ ወይም ሸይጧን እና ወጥመዶቹ

Author picture
ኢብሊስ ወይም ሸይጧን ጭስ አልባ ከሆነ እሳት የተፈጠረ ሲሆን መላኢካ ባይሆንም ለአሏህ በነበረው ታዛዥነት ግን በጀነት ከነሱ መካከል ነበር። ሰይጣን ወይም ጋኒን ተብሎም ይጥራል። ኢብሊስ ከፍ ያለ ደረጃ ነበረው።
ኢብሊሰ ወይም ሸይጧን

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ፋጢር 35:6)

በእርግጥ ሸይጧን ላናንተ ጠላት ነው። እናም ጠላት አድርጋችሁ ያዙት። ተከታዮቹን የሚጣራው ከዕሳት ጏደች እንዲሆኑ ብቻ ነው።

የኢብሊስ (የሸይጧን) ታሪክ በጨረፍታ

እኔን ከእሳት ፈጠርከኝ

ኢብሊስ ወይም ሸይጧን ጭስ አልባ ከሆነ እሳት የተፈጠረ ሲሆን መላኢካ ባይሆንም ለአሏህ በነበረው ታዛዥነት ግን በጀነት ከነሱ መካከል ነበር። ሰይጣን ወይም ጅን ተብሎም ይጥራል። ኢብሊስ ከፍ ያለ ደረጃ ነበረው።

ከጭቃ ፈጠርከው

አሏህ ሸይጧንን የፈጠረው ከእሳት ነው። ቅዱስ ቁርአን እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አዕራፍ 7፡12)

ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ አለው። እኔ ከእሱ የበለጥኩ ነኝ። እኔን ከእሳት ፈጠርከኝ፤ እሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ።

ሸይጧን የሚለው የአረብኛ ቃል የመጣው ሸጣና ከሚለው ስረወ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ልዩ መሆን ወይም መቃረን (መቃወም) የሚለው ነው።

የሸይጧን ተፈጥሮ ከሰው ልጆች የተለየ ነው። ከክፋቱ ብዛት ሁልጊዜ መልካም ነገሮችን እንደተቃወመ ነው።

በአረብኛ ቋንቋ አመጸኛ የሆነ ፣ መልካም ነገር የሚቃረን ሰው ሸይጧን ተብሎ ይጠራል። አሏህ እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አንዓም 6፡112)

እንደዚሁም ለነብያት ሁሉ ከሰውና ከጋኔን የሆኑ ሰይጣናት ጠላት አደረግን።

የመልአክቶች ጓድም ነበር። አሏህ (ሱ.ወ.ተ) አደም (ዐ.ሰ) በፈጠረ ጊዜ ጀነት ወሰጥ ያሉ ሁሉ ከአደም (ዐ.ሰ) ፊት ለፊት ይሰግዱ አዘዛቸው።

ነገር ግን ሸይጧን በእብሪተኝነት እና በኩራት አሻፈረኝ አለ፡፡ ኢብሊስ በእብሪተኝነት እንዲህ ማለቱን ቁርአን ይናገራል

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ሷድ 38፡76)

እኔ ከእሱ የተሸልኩ ነኝ። እኔን ከእሳት ፈጠርከኝ፤ እሱን ደግሞ ከጭቃ ፈጠርከው አለ።

አሏህ ሲቀጣው የመለአክት ጓድነትን ነጠቀው፤ ረገመውም። ኢብሊስ ከመልአክቶች ጓድነት ከተባረረ በኋላ ሰዎችን ለማጥመም ዛተ።

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ሷድ 38፡82-83)

(ኢብሊስ) አለ፤ በልቅናህ ይሁንብኝ ሁሉንም አጠማቸዋለህ። ከባሮችህ መካከል ሙህሊሶች (አሳማሪዎች) ሲቀሩ።

አሏህም ሸይጧንን ረግሞት ከጀነት አባረረው። ሆኖም ግን ሰዎችን የሚያጠምበትን እድል ይሰጠው ዘንድ ጠየቀ፤ አሏህም የጠየቀውን ነገር ሰጠው።

አል-ቁርአን

{ሱረቱል አዕራፍ 7:16-17}

ስለአጠመምከኝ ለእነርሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ በእርግጥ እቀመጥባቸዋለሁ አለ። ከዚያም ከስተፊቶቻቸው ፣ ከኋላቸው ፣ ከቀኛቸውና ከግራቸው በኩል በእርግጥ እመጣባቸዋለሁ። አብዛሃኛዎቹንም አመስጋኝ ሆነው አታገኛቸውም አለ።

ኢብሊስ የሰው ልጅ ጠላት ነው። ምክኒያቱም የአሏህን ትዕዛዝ እንዲጥሱ መጥፎ ሃሳቦችን ለእነሱ ስለሚያንሾካሹክ።

በእርግጥ አደም እና ሐዋ የተፈተናቸው እና ያሳሳታቸው ኢብሊስ ነበር።

የእናንተ ቅን መካሪ ነኝ ብሎ በመግለፅ ፣ አሏህ እንዳይቀርቡ ያዘዛቸውን ዛፍ እንዲቀምሱ በማታለል እና በማሳመን ያሳሳታቸው እሱ ነውና። እናም ውድቀትን አከናነባቸው።

ሸይጧን የሰው ልጅ ጠላት ነው። አደምና ሐዋ አሏህን እንዳይታዘዙ (እንዲያምፁ) በማድረግ ከጀነት የመባረራቸው ምክኒያት ሆኗል።

የአደምን ልጆች ለማሳሳት እና ለማጥመም ምሏል። ቀን እና ማታ የሚፈትናቸው በጎን ነገር እንዲተው መጥፎ ነገር እንዲሰሩ የሚጎተጉታቸው ለዚሁ ነው።

ሆኖም ሙስሊሞች ሁሌም ከተረገመው ሸይጧን ክፋት የአሏህን ከለላ መፈለግ እና በእሱ መጠበቅ አለባቸው። አሏህ እንዲህ ይላል፡

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አዕራፍ 7፡200-201)

ከሰይጣንም ጉትጎታ ቢያገኝህ በአሏህ ተጠበቅ። በእርግጥ እሱ ሁሉን ሰሚ ሁሉን አዋቂ ነውና። እነዚያ ሙተቆች ከሸይጧን ጉትጎታ ባገኛቸው ጊዜ አሏህን አስታዋሾች ናቸው። በእርግጥ እነሱ ይመለከታሉ።

በዚህም ምክኒያት እንደፈለጉ በመለካም ነገሮች ከሚደሰቱባት ገነት ተባረሩ። ይሁን እንጅ የአሏህን ምህረት ለመኑ፤ ማራቸውም።

ኢብሊስ የእኛ ጠላት መሆኑን አሏህ አሳውቆናል። ከፈተናዎቹም አስጠንቅቆናል።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል በቀራ 2፡168)

የሸይጧንን ኮቴ አትከተሉ፤ በእርግጥ እሱ የእናንተ ግልፅ ጠላት ነው።

የሸይጧን ወጥመዶች

የአምላክ አንድነትን የማስካድ ስልት

እንደሚታወቀው የእስልምና ሃይማኖት መሠረቱ ተውሂድ ወይም አሃዳዊነት ነው። ይህም አሏህ የዚህ ዩኒቨርስ ፈጣሪና አስተናባሪ ፣ ሰጭ ፣ ነሽ መሆኑን እንዲሁም የአምልኮት ተግባራት በሙሉ ለአሏህ ብቻ ማድረግንና ልዩና ውብ የሆኑ ስሞችና ባህሪያቶች እንዳሉት ማረጋገጥ እና ማመን ነው።

ከዚህ በተቃራኒ ከአሏህ ዘንድ ከበደሎች ሁሉ የከፋ በደል ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ወንጀል ብሎ ማለት በአሏህ ላይ ማጋራት ሽርክ ነው። ለምሳሌ፦

  • የአምልኮት ተግባራትን ከአሏህ ውጭ ላሉ ነገራት ማድረግ (ከአሏህ ውጭ የሆኑ ነገሮችን መለመን ፣ ለነሱ ማረድ ፣ መስገድ ፣ በነሱ መመካት ወ.ዘ.ተ)
  • የአሏህን ስምና ባህርያት አለመቀበል ወይም በፍጡራኖቹ መመሰል ትርጉማቸውን መቀየር ወ.ዘ.ተ
  • አሏህ ልጅና እናት አለው ወይም ደግሞ ሌላ ባላንጣ አለው ብሎ ማመን

የሸይጧን ዋና ግቡ የሰው ልጆችን ማጥመም ሲሆን ነገርግን ሸይጧን ግልፅ የሆነ ክህደቶችን እንዲፈፅሙ ማድረግ ካልቻለ ሌላ አማራጮችን ይጠቀማል።

ለምሳሌ የሩቅን አዋቂ አሸናፊ ጥበበኛ አሏህ ብቻ ሆኖ ያለ ሰዎች በጥንቆላ ፣ በድግምት ፣ በኮኮብ ቆጠራ ወ.ዘ.ተ እንዲያምኑ ለማድረግ ይሞክራል።

በዲነል ኢስላም መሠረት የሌላቸውን ነገሮች እንድንፈላሰፍና ቢድአ ነገሮችን እንድንሰራ የማድረግ ስልት

ሌላኛው የሸይጧን ሴራ ሰዎች የተሳሳተ አቂዳ በኢስላም እንዲይዙ ማድረግ ሲሆን ይህም አሏህ (ሱ.ወ.ተ) እና መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ያልደነገጉትን ነገር መስራት ነው።

በሌላ አገላለፅ የእምነቱን ክፍል የሚጣረሱ ነገሮችን ከራስ ፍላፍልስፍናና ስሜት በመነሳት ያልነበሩ ነገሮች የዕምነቱ ክፍልና የአዕምኮት ተግባራት አድርጎ መያዝን ያስከትላል።

በእርግጥ እነዚህ የቢድአ ሰዎች ኢስላም በራሱ ሙሉ እንዳልሆነ በማመን ወይም መለኮታዊ ራዕይ በትክክል እንዳልተገለፀ በማመን ወደ ቢድአ ነገራቶች ይዘምታሉ።

ይህ ግን ግልፅ የሆነ ኩፍር ወይም ክህደት ነው። ምክኒያቱም አሏህ የገለፀውን ነገር መካድ ነውና። አሏህ በቁርአኑ በሱረቱ አል-ማኢዳ አንቀፅ 3 ላይ እንዲህ ይላል

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ማኢዳ 5:3)

ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ፀጋየንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፤ ለናንተም ከሃይማኖት በኩል ኢስላምን መረጥኩ።

ግዴታ የሆኑ ስራዎችን ችላ የማስባል ስልት

አሏሁ አዘወጀል በቁርአኑ በሱረቱል ማኢዳ አንቀፅ 91 ላይ እንዲህ ይላል

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ማኢዳ 5:91)

ሸይጧንም የሚፈልገው አሏህን ከማውሳትና ከሶላት ሊያግዳችሁ ብቻ ነው።

አሏህ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ የተወሰኑ ስራዎችን ግዴታ ያደረገ ሲሆን ለጊዜው አምስት አውቃ ሶላቶችን መጥቀስ በቂ ነው።

ሸይጧንም ብዙ ሃጢያቶችን እንድንሰራ በመሻት ሶላቶቻችነን ችላ እንድንልና ብሎም ከሶላት እንድንርቅ ለማድረግ ይሞክራል።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል ዓንከቡት 29:45)

እነሆ ሶላት ከመጥፎና ከተጠላ ነገር ከልካይ ናት።

ቀስበቀስ የማጭበርበር ስልት

እንዴት የጣዖት አምልኮት እንደተጀመረ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የገለፁልን ሲሆን ይህም በሸይጧን ትዕግስትና የቀስበቀስ የማጭበርበር ዘዴ ነበር።

በነብዩሏህ ኑህ (ዐ.ሰ) ዘመን የነበሩ ሷሊህ ሰዎች ከሞቱ ብኋላ ሸይጧን መጣና ደግነታቸውን ለማስታወስና ለክብራቸው ሃውልት በዙርያችሁ ይቁምላቸው ሲል ገፋፋቸው። ያ ትውልድ ባለፈ ጊዜ ሰዎች ሃውልቶቹ ለምን እንደቆሙ ረሱ።

ሸይጧንም የአባቶቻችሁ አባቶች ያመልኳቸው ነበር፤ በነርሱም ምክኒያት ዝናብ ይጥል የነበረው ሲል አጭበረበራቸው። ሰዎቹም እነዛን ሃውልቶች ማምለክ ጀመሩ።

ይህ ቀስበቀስ የማጭበርበር ዘዴ በብዙ መንገድ ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ሰዎች ዝሙት ይፈፅሙ ዘንድ አጅነብይ የሆነችን ሴት (ወንድ) እንድንመለከት በማድረግ ይጀምርና ስለሷ እንድናስብ ብሎም ፈገግ እያልን እንድንስቅ እንድንጫወት ይጋብዘናል።

በመጨረሻም ብቻችነን ተገናኝተን እንድናወራ በመጋበዝ የከፋ ሃጢያት ላይ ይጥለናል።

በተመሳሳይ መልኩ ሱና ሶላቶቻችነን እንድንተው በተለያዩ በማይረቡ ምክኒያቶች ያሳምነንና ከዛም ግዴታ የሆኑትን ሶላት እንዳንሰግድ ያዳክመናል። ይህን ተከትሎም ግዴታ ሶላቶቻችነን እስከመተው ወይም ችላ እሰከማለት እንደርሳለን።

መጥፎ ተግባራትን የማስዋብ ስልት

ሸይጧን ሃጢያት ነገሮችን አስውቦ ለሰዎች ያቀርባል። አደምና ሐዋን በዛች ከበደለኞች በምታደርጋቸው ዛፍ እንዴት እንዳታለላቸው ማስታወስ በቂ ነው። ሸይጧን ለአደም (ዐ.ሰ) እንዲህ ሲል ሹክ አለው

አል-ቁርአን

(ሱረቱ ጧሃ 20:120)

አደም ሆይ! ህያው(ዘላለማዊ) ወደ ምታደርግህ ዛፍና ዘላለማዊ ወደሆነው ግዛት አላመላክትህምን? አለው።

ብዙ ሐላል የነበሩ ምግቦች በአደም (ዐ.ሰ) ዙርያ ቢኖርም ሸይጧን ግን ከዛች ሐራም ከሆነች ዛፍ እንዲመገብ ገፋፋው።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አንዓም 6:43)

ይጠሉት የነበሩትንም ነገር ሸይጧን አሳመረላቸው።

ሸይጧንን እንዴት ማሸነፍ እንችላለን

በመጀመሪያ ደረጃ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ሸይጧን የኛ ግልፅ ጠላት መሆኑን መገንዘብና ጠላት አድርገን መያዝ ነው። የጠላታችነን ማንነት ካወቅን ያኔ እሱን ማሸነፍ እንችላለን።

ከሸይጧን በአሏህ የምንጠበቅበት አንደኛው መንገድ “አኡዙ ቢላሂ ሚነሸይጧኒ ረጅም (ከተረገመው ሸይጧን በአሏህ እጠበቃለሁ)” ማለት ነው።

የሸይጧን ሃይል ወይም አቅም ያለው የማታለል ብቃቱ ላይ ነው። ሆኖም እራሳችነን ከሸይጧን ተንኮል ለመጠበቅ የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ስልቶች እንዲሁም የተለያዩ ዘዴዎቹን መረዳት ይኖርብናል።

የአሏህ እርዳታን መሻት

የአሏህን ጥበቃና ከለላ መለመን እንዲሁም በሱ ላይ መመካት ሸይጧንን ማሸነፊያ አይነተኛ መሳሪያ ነው። ሱረቱል አል- ፈለቅና ሱረቱ ናስ አዘውትረን በመቅራት ከሸይጧን ተንኮል በአሏህ መጠበቅ እንችላለን።

ሆኖም ግን በህይወት እስካለን ድረስ ሸይጧን መቼም ቢሆን እጅ አይሰጥም፤ እኛን ለማጥመም ደከመኝ ሰለቸኝ አይልም። ስለዚህ ዘወትር አሏህ ይመራንና ይጠብቀን ዘንድ እሱን መለመን ይኖርብናል።

የአሏህን ምህረት መለመን

በሸይጧን ሴራ ከተሸነፍን በአሏህ እዝነትና ቸርነት ህይወታችነን የምናስተካክልበት ሌላ እድል አለን።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

{አህመድ}

የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሸይጧን ለሃያሉ አሏህ (ሱ.ወ.ተ) እንዲህ አለ “አምላክ ሆይ በልቅናህ ይሁንብኝ ባሮችህን ለማጥመም መሞከሬን እቀጥላለሁ ነፍሳቸው በአካላቸው እስካለች ድረስ” አለ። ጌታ(አሏህ) “በልቅናየ ይሁንብኝ ምህረቴን እሰከለመኑኝ ድረስ እነሱን መማር እቀጥላለሁ አለ” ብለዋል።

ተውበት ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ቅንና እውነተኛ እንዲሁም ከልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል።

እንዲሁም ያን ወንጀል ወይም ሃጢያት ደግሞ ላለመፈፀም ማሰብንና ቆራጥ ውሳኔን መወሰን ይጠይቃል።

ከወንጀል ተግባራቶች መራቅ

አሏህ (ሱ.ወ.ተ) ከዛች ዛፍ በከለከለው ጊዜ ከዚህ ዛፍ አትብላ አይደለም ያለው። ይልቁንም በሱረቱል በቀራ አንቀፅ 32 ላይ እንደገለፀው “ወደዚህ ዛፍ አትቅረቡ” ሲል ነበር የከለከለው።

ስለዚህ ወንጀል እንድንፈፅም ከመሚመሩን ነገሮች በሙሉ እራሳችንን ማራቅ ይኖርብናል ማለት ነው።

እኛ ወጣቶች እንደመሆናችን መጠን ብዙ ጊዜ በጏደኞቻችን ተፅዕኖ ስር እንወድቃለን። ሆኖም ጓደኞቻችን መጥፎ ከሆኑ የኛም ማንነት የጓደኛችነን ማንነት ነው ሊመስል የሚችለው።

ስለዚህ መጥፎ ጓደኛ አሏህን ወደ ማመፅ እንጅ ወደ ኸይር ነገር ስለማይመራ የኛ ምርጫ አሏህን የሚታዘዝ ፣ የከለከለውን ነገር የሚከለከል ፣ መልካም ነገር እንድንሰራ የሚያበረታታን መሆን ይኖርበታል።

አል-ቁርአን

(ሱረቱል አዕራፍ 7:200)

ከሰይጣንም ጉትጎታ ቢያገኝህ በአሏህ ተጠበቅ። እርሱ ሰሚም አዋቂም ነውና።

መልካም ስራዎችን እንስራ

በመልካም ስራዎች ግዜያችነን ካሳለፍን ለመጥፎ ስራዎች ቦታ አይኖረንም። እንዲሁም በሸይጧን ሴራ በቀላሉ ከመሸነፍ እንድናለን።

አሏህ ሃጢያቶቻችነን ይምረን ዘንድና ከሸይጧን ወጥመዶች ይጠብቀን ዘንድ ውብ በሆኑ ስምና ባህሪያቶቹ እለምነዋለሁ።

Related posts

እስልምና እና እውቀት

የእስልምና ሃይማኖት ሁሉም ሰዎች እውቀት እንዲፈልጉ እና እውቀታቸውን እንዲጨምሩ ያበረታታል። ድንቁርናን ያወግዛል እንዲሁም ያስጠነቅቃል። አላህ እንዲህ ይላል፡- እውቀት መፈለግ ፣ መማር እና ማስተማር ወደ ጀነት

Read More »

እስልምና የሰላም ሃይማኖት

እስልምና ማለት ለአላህ መታዘዝ ፣ ትዕዛዙን በመፈጸም ላይ ጽናት ማሳየት፣ ከአላህ ሌላ ማንኛውንም አካል ከማምለክ ነፃ መሆን ማለት ነው።

Read More »
እስልምና እና ማህበረሰብ

እስልምና እና ማህበረሰብ

እስልምና አካባቢን እንድንከባከብና እንድንጠብቅ ያዛል። በዚህም ምክንያት እስልምና በምንም መልኩ አካባቢን መበከል ይከለክላል። ጠቃሚ እፅዋት እና ዛፎችን መትከል ያበረታታል።

Read More »
እስልምና እና ጅሃድ

እስልምና እና ጅሃድ

በእስልምና ውስጥ በብዛት ሰዎች ከሚሳሳቱባቸው ቃላት አንዱ “ጅሃድ” የሚለው ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ “ጅሃድ” የሚለው ቃል አላግባብ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ከጦርነት እና

Read More »

Share